Thursday, April 19, 2012
Wednesday, April 18, 2012
የመለስ የማጥቃት ስትራቴጂ
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመምህራን ጥያቄ ላይ የዘገየ
መልስ ለመስጠት ወደ ፓርላማው ጎራ ብለው ነበር። ይህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመምህራኑ የተሰነዘረው የመልስ ምት አላማውን እና ግቡን
የሳተ ነበር። እንደ ሌሎቹ ሃገራት ቢያድለን እና መምህራኑ ጥያቄ ባነሱበት ወቅት አፋጣኝ ምላሽ ቢሰጡ ኖሮ የማጥቃት ስትራቴጂያቸው
ላይ ጥያቄ ባላነሳን። የሆነ ሆኖ በመምህራኑ የተነሳው ጥያቄ ላይ መድፋቸውን ተኩሰው መምህራኑን አቁስለው በጉልበት ካንበረከኩ በሁዋላ
መድረኩ ላይ ወጥተው ማቅራራታቸው ትዝብት ውስጥ ይከታቸዋል እንጂ በጀ አያስብላቸውም።
ስለ አቶ መለስ ባሰብኩ ቁጥር ሁሌም የሚገርመኝ ወቅታዊ በሆኑ
ጉዳዮች ላይ የቁጥር ስሌታቸው ነው። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በተመለከተ 11 ነጥብ ላይ ተንጠልጥለዋል። በምርጫው ደግሞ 99.6 ሲሉ
ክችች ብለዋል። አሁን ደግሞ በብዙሃን መምህራን የተነሳውን ጉዳይ ከአንድ ፐርሰንት ያነሱ በማለት ህዝባቸውን ሊያምታቱ ሞክረዋል።
በነገራችን ላይ አቶ መለስ የስራ ማቆም አድማ ያደረጉት መምህራን ከ500 የሚበልጡ አይደሉም ሲሉ ቢሳለቁም ቁም ነገሩ 500 ወይም
አምስት መሆኑ ሳይሆን ጥያቄው መነሳቱ በራሱ ሊያስደነግጣቸው በተገባ። የስመ ጥሩው ኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤት መምህራን በሙሉ ጥያቄ
ማንሳታቸው ብቻ ትልቅ ሃገራዊ ጉዳይ በሆነም ነበር። በመለስ የቁጥር ስሌት አምስት ሆነ አምስት መቶ ወይም 99.9 እያሉ እውነታው
ላይ ከመዘባበት የመምህራኖቹ ጥያቄ ምን ነበር ብሎ በሰከነ ልቦና ማድመጥ በተገባቸው ነበር።
የአቶ መለስ ሌላኛው ባህሪ የእኔ ተቀናቃኝ
ነው ብለው ያሰቡትን ወይም ጥያቄ ያነሳባቸውን ሁሉ ከኦነግ፣ ግንቦት 7 እና ከሻእቢያ ጋር የመደመር አባዜያቸው ነው። እነዚህ ድርጅቶች
በተኙበት ሳይቀር የሚያቃዥዋቸው አስመስሎባቸዋል። ምንም እንኳን “መለስ ከልጅነት እስከ እውቀት” በሚለው መጽሃፍ ላይ “ሁሌም ከእንቅልፍ የሚያባንነኝ ስጋት አለ ይቺ ታላቅ
ሃገር ከአንድ ሺህ አመት በፊት ታላቅ የነበረች ሃገር አስከፊ አዘቅት ውስጥ ገብታ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ የተራቡባት እና የሞቱባት
ሃገር ምናልባት በመፈረካከስ ላይ ትሆን? የሚል ፍርሃት ከእንቅልፌ ይቀሰቅሰኛል” ቢሉንም ቅሉ አሸባሪ ሲሉ የሰየሟቸው አባናኝ ሆነውባቸዋል።
በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ግብ የለሸ መሆን የሚያሳየው
የመምህራኖቹን ጥያቄ መልሰው እራሳቸው ማስተጋባታቸው ነበር። “የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ የኛን ህይወት የሚቀይር አይደለምና ይህንን
የተናገሩት የመንግስት ባለስልጣናት ማስተባበያ ይስጡ” ሲሉ መምህራኖቹ ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን እንዳንረሳው ገና ሁለት ሳምንት
አልሞላንም። አቶ መለስም “ያደረግነው የደመወዝ ጭማሪ ሳይሆን የእርከን ማስተካከያ ነው ይህ ደግሞ የመምህራኑን ህይወት አይቀይርም”
ሲሉ ተደምጠዋል። ታድያ አቶ መለስ በዚህ ጉዳይ ላይ ከተስማሙ የመምህራኑ ወንጀል ምኑ ላይ ነው? አቶ መለስ አስቀድመው ከራሳቸው
ጋር በሰከነ ልቦና መምከር በተገባቸውም ነበር። ምክንያቱም ኢቲቪ ለመምህራን የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ የመምህራኖቹን ህይወት የሚለውጥ
ነው ማለቱን እረስተውት ወይም አልተመለከቱት ይሆን?
የአቶ
መለስ ንግግር በጥሞና ላዳመጠ “እኚህ ሰውዬ የሚኖሩት በተለየ አለም ነው እንዴ?” የሚያስብል ነው። የስራ ማቆም አድማ ያደረጉት
መምህራን የማስተማር ብቃት የሌላቸው ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል። እንግዲህ ስራ በቆመባቸው ትምህርት ቤቶች የነበሩት መምህራን ላይ የብቃት
ጥያቄ ከተነሳ በነዛ ትምህርት ቤቶች ትምህርት የቆመው መምህራኖቹ ጥያቄ ሲያነሱ አልነበረም ማለት ነው። መለስ ከጫካ አስተሳሰብ
ወጥተው እንደ ሃገር መሪ ማሰብ በተገባቸው ነበር። ይህንን ማድረግ ባይችሉ እንኳን ለፓርላማቸው ክብር ቢኖራቸው መልካም ነበር።
Tuesday, April 17, 2012
Monday, April 16, 2012
የፍትህ መንገድ-ከአሲምባ እስከ ቀራኒዮ
ተመስገን ደሳለኝ
አቤት! እንደምን ያለ ጉዞ ነው? አድካሚ፣ ፈታኝ፣ አስፈሪ፣ አደናቃፊ… ብቻ ዙሪያው በአደጋ የተሞላ ነው። ልክ እንደ ጦር ሜዳ። በእርግጥ ጦር ሜዳን በፊልም እና በቴሌቪዥን ካልሆነ ገፅ-ለገፅ አይቼ አላውቅም። ሆኖም በጣም አስፈሪ እና ከሞት ጋር ‹‹አኩኩሉ›› የመጫወት ያህል እንደሆነ ለማወቅ አይቸግረኝም።
ለዚህም ነው በጦር ሜዳ ‹‹ሞት እርካሽ ነው›› ሲባል ግነት እንዳይመስልህ የምልህ። ምንአልባት ከጎኑ ከሻጠው ኮዳ ውሃ ያስጎነጨህ ጓደኛህ ኮዳውን ከመመለስህ በፊት ሞቶ ወይም ሊሞት ሲያጣጥር ልታገኘው ትችላለህ። ለምን? በቃ! በጦር ሜዳ ሞት ከአይነ እርግብግቢት የፈጠነ ነዋ። የጦር ሜዳን መከራ ይበልጥ የሚያበዛው ደግሞ ላለመሞት የሚደረገው ግብግብህ ከጠላት ጋር ብቻ አለመሆኑ ነው። ከወገንም በኩል የሚነሳ የሞት መልዕክ አለና።
እናም ድንገት ወደ ውጊያ ከመግባትህ በፊት የተጠመደ ፈንጅ ታከሽፍ ዘንድ አለቃህ ይመርጥሃል። (ወዳጄ ‹‹ይመርጥሃል›› ስልህ ለሹመት እንዳይመስልህ፣ በፈንጂ ላይ ተረማምደህ ስጋና አጥንትህ ተበጣጥሶ ለሌሎች ወታደሮች መንገድ ትጠርግ ዘንድ ነው-የመረጠህ) አየህ! በጦር ሜዳ ሞት የቅርብ ጓደኛህ ብቻ ሳይሆን ጥላህም ነው። ጥላ ደግሞ ስትሄድ ይሄዳል፣ ስትቆም ይቆማል። ሞትም እንዲያ ቅርብ ነው።
ዛሬ የምተርክልህ የጉዞ ገድልም ከዚህ በማይተናነስ መልኩ በአደጋ የተሞላ ነው ስልህ እመነኝ አላጋነንኩትም። በፈንጅ የታጠረ ነው። ይህን ከጦር ሜዳው ፈንጅ ወረዳ የሚለየው እንደ ጦር ሜዳ ፈንጅ መቀበሩን የምታውቀው ጓደኛህ ተንከባሎበት ሲበጣጠስ አለማየትህ ብቻ ነው። እዚህ በግልፅ በመንግስት ሚዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ‹‹አሁን ቀዩን መስመር አልፈሃል››፣ ‹‹11ኛው ሰዓት ላይ ደርሰሀል››… ይሉሀልና። ያን ጊዜም ሁለት ስሜቶች ይፈጠሩብሃል ‹‹መራድ›› ወይም ‹‹በጽናት መቆም››፡፡ ግና የምትጓዘው ለሀገርና ለህዝብ እስከሆነ ድረስ ለምን ትርዳለህ? ጥያቄው ይህ ነው፣ መልሱም በእጅህ ነው።
ፍትህ ስትመሰረት ምንም አልነበረም። በመስራቾቿ እጅ ማለቴ ነው፡፡ ነገር ግን ከምንም በላይ አንድ ነገር ነበረን። አላማ የሚባል፡፡ ያ አላማ መኖሩ ነው፣ የፍትህን ጅማሮዋን ብቻ ሳይሆን መጨረሻውንም አውቀን እንድንግባ ያደረገን። እናም ስንጀምር መድረሻችንን እናውቀዋለን። መንገዳችንም በመሰናክል ናዳ የተሞላ ሊሆን እንደሚችል እናውቃለን፡፡ መጓዛችን አይቀሬ እንደሆነም እናውቃለን፡፡ ከቶም ምንም ነገር ከመድረሻችን ሊመልሰን እንደማይችል እናውቃለን፡፡ እስርም፣ ሞትም፣ ጫናም... ፡፡ ለነገሩ እነዚህ ሁሉ ከሀገር እና ህዝብ በታች ናቸው። እናም እልሀለሁ ጉዳዩ የሀገር እስከሆነ ድረስ፣ ተጠቃሚው ህዝብህ መከራውም ስለምትውዳት ሀገር እስከሆነ ድረስ የመረጥከውን መንገድ ይዘህ መጓዝ እንጂ የምትከፍለው ዋጋ ሊያሳስብህ አይገባም።
በእርግጥ የፍትህ ፈተና ይህ ብቻ አይደለም፣ ከዚህም ይሻገራል። ነባር የፍትህ አንባቢዎች እንደሚያስታውሱት ፍትህ ቀኗን ጠብቃ ለንባብ የማትበቃበት ጊዜ ነበር። ለአራት ሳምንት ያህል ያልታተመችበት ጊዜ ሁሉ አለ። በቂ የገንዘብ አቅም አልነበራትምና። በአናቱም ያች ሚጢጢዋ የፍትህ ቢሮ ከአንዴም ሁለቴ ተዘርፋለች። የሁለተኛው ዝርፊያ ለፖሊስ ቢመለክትም እስከዛሬም ድረስ ዘራፊዎቹን አየን ያለ የለም።
ሌላው ፈተና ደግሞ ከቤተሰብህ እና ከወዳጆችህ የሚመጣው ጫና ነው። ሆኖም እንዲህ አይነቱን ፈተና በቀላሉ ማለፍ ትችላለህ። ‹‹ይቅርብህ፣ ተው…›› ለሚሉህ እናትና አባትህ አሊያም ሌሎች የቤተሰብ አባላት ‹‹ከሀገር አትበልጡም›› ብለህ በመመለስ ማለቴ ነው። ይህም አልገባቸው ካለ እንዲህ ስትል ዘምርላቸው፡-
እናት አባት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል
እህት ወንድም ቢሞት በሀገር ይለቀሳል
ሀገር የሞተ እንደው ወዴት ይደረሳል…
አዎን! ወዴትም አይደረስም። እንዲሁም እንዲህ ብለህ አትፃፍ፣ መንግስት ሀይለኛ ነው፣ ፖለቲካ ኮረንቲ ነው፣ ገለመሌ ለሚሉ ወዳጅ ዘመድ ደግሞ ከህገ-መንግስቱ ውስጥ ሀሳብን ያለገደብ መግለፅ እንደምትችል የሚፈቅደውን አንቀፅ ድምፅህን ከፍ አድርገህ አንብብላቸው። ከፍ አድርገህ…
የሆነ ሆኖ ነገ ድፍን አራት አመት የሚሞላት ፍትህ እዚህ የደረሰችው በ‹‹መራድ›› እና በ‹‹መጽናት›› ወጀብ ከወዲህ ወዲያ እየተላጋች ነው። በእርግጥ እንዲህ ያለው አድካሚ እና ፈታኝ ጉዞ ነገም ይጠብቃታል። አደጋውን አስፈሪ የሚያደርገው ደግሞ ከቀን ወደ ቀን የመሰናክሉ አይነት መጨመሩና መደደሩ ነው።
ማን ነበር ህዝቡን ከረጅም ጉዞ በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር ያደረሰው? ሙሴ ይሆን? የለም የለም የሙሴ ጉዞ ለእኛ አርዕያ አይሆነንም፡፡ ሙሴ የታገለው ‹‹ህዝቤን ልቀቅ›› ብሎሃል እያለ ነውና፡፡ የእኛ እንዲህ የሚል መዕልክት አስተላለፊ ‹‹ኃይለኛ›› የለውም፡፡ ያለው ይህ የኔ ትውልድ (እኔና አንተ) ነው፡፡ እናም እኛው ራሳችን ነን ‹‹በቃን! ልቀቁን›› እያልን ያለነው ወይም የምንለው፡፡ ታዲያ ማን ይሆን ህዝቡን ከረጅም ጉዞ በኋላ ‹‹ከንአን›› ያደረሰው? የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ መስራቾች ናቸው ብትል አልዋሸህም፡፡ ነገሩም እንዲህ ነው፡-
ከዛሬ 80 አመት በፊት CCP የተባለው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ፣ ከወቅቱ የቻይና ገዢ ፓርቲ “Kuomintang” ጋር ለህግና ለስርዓት ያስቸገሩትን በመላ ቻይና የነበሩ የጦር አበጋዞችን በትብብር ድራሻቸውን ለማጥፋት ይስማማል። በስምምነታቸው መሰረትም በየአጥቢያቸው ትናንሽ ንጉስ ሆነው አልገዛም ያሉትን የጦር አበጋዞች ከግራና ቀኝ አጥቅተው ያጠፋሉ። ከዚህም በኋላ ኮሚኒታግ ቃሉን አጥፎ የተቆጣ ፊቱን ወደ CCP ያዞራል። ይህን ግዜ የመንግስት ሀይል ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ የገባቸው ማኦ ዜዱንግ እና ጓደኞቹ ከከተማ ወደ ገጠር ሸሹ። ዛሬ በቻይናዊያን እንደገድል የሚነገርለትን Long march (ረዥሙ ጉዞን) በዚህ አስገዳጅ ሁኔታ ነው CCP የተጓዘው። የጉዞውም እርቀት 11 ሺ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። ከዚህ በኋላም CCP ራሱን አጠናከረ። የጥንካሬያቸው ምንጭ ደግሞ ለአንድ አመት ያህል በፈጀው ጉዟአቸው የሚበሉት አጥተው መርዛማ ቅጠል እየበሉ ሳይቀር መጓዛቸው ብቻ ሳይሆን ከጉዞው በኋላ ያደረጉት ስር ነቀል ተሀድሶ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ነው CCP በድል እየገሰገሰ በሽንፈት ለቆት ወደሄደው ከተማ የተመለሰው። እነሆ ያ ፓርቲ ዛሬም በስልጣን ላይ አለ። ምን አልባት፣ ምንአልባት ግን በዛ አስቸጋሪ ጉዞ ቢበገር ኖሮ፣ ዛሬ CCPን እንኳ እኔና አንተ ምሳሌ ልናደርጋቸው ቀርቶ ቻይናውያንም አያውቁትም ነበር። ይህ ነው አይበገሬነት።
ሌላም በፈተና ከተሞላ ጉዞ በኋላ ታሪክ የሰራ ድርጅት አለ፤ ህወሓት። ህወሓት ለ17 አመት ያህል ተጉዟል። ያውም በመሳሪያ፣ በሰው ሀይል እና በስልጠና በእጅጉ ከሚበልጠው ከቀድሞ መንግስት ወታደሮች ጋር እየተዋጋ። እናም ብዙ የገደለ ሞትን ያሸንፋል እንዲሉ ህወሓትም ከዚህ ሁሉ ጉዞ በኋላ የመንግስቱን መንበር ያዘ። ነገር ግን የህወሓት ጉዞ እንደ CCP የተሳካነው ማለት አንችልም። ምክንያቱ ደግሞ ከህወሓት መስራቾች አብዛኞዎቹ ዛሬም በሌላ ረጅም፣ አሰልቺ እና ፈታኝ ጉዞ ላይ መሆናቸው ነው። …አረጋዊ በርሄ፣ ግደይ ዘራዕፅዮን፣ ስዬ አብርሃ፣ ገብሩ አስራት፣ አወአሎም ወልዱ፣ አረጋሽ አዳነ፣ አስገደ ገብረሥላሴ፣ አለምሰገድ ገ/አምላክ… ህወሓትን መስርተው የ17 አመቱን ጉዞ የመሩ ናቸው። ሆኖም ዛሬም በሌላ ጉዞ ላይ ይገኛሉ። ህወሓትን ይዘን የተጓዝነው ጉዞ የስህተት ጉዞ ነው በሚል ማለቴ ነው። እንደምራቂ ደግሞ የህወሓት የአማርኛ ተናጋሪ ክንፍ የሆነውን ብአዴንንም ብታየው ከላይ የነበረው አመራር አሁንም በአዲስ ጉዞ ላይ ነው። በእርግጥ የብአዴን ሰዎች እየተጓዙ ነው ስልህ የታምራት ላይኔንም ጉዞ ከዚህ እንዳታያይዘው፡፡ የእርሳቸው ለፅድቅ ነውና፡፡ መሰረቱም ምድራዊ ሳይሆን ሠማያዊ ነው፡፡ ምንጩም ፖለቲካ አይደለም፤ የእስር ቤት ‹‹ራዕይ›› እንጂ፡፡
ፍትህ ስትመሰረት ረጅምና የፈተና ጉዞ እንደሚጠብቃት መስራቾቿ ያውቁ እንደነበር ተነጋግረናል፡፡ አውቀውም ነው የገቡበት ብዬሀለሁ፡፡ ሆኖም ፍትህ እንዲህ ሄዳ ሄዳ ብቻ የመሆን ዕዳ ላይ ትወድቃለች የሚል እሳቤ ግን አልነበራቸውም። የሆነው ግን እንዲያ ነው። የተለያዩ የሚታዩና የማይታዩ አደጋዎችን ተቋቁማ፣ አንዳንዴም እየተቸነከረች፣ አንዳንዴም እየተሸራረፈች ዳገቱን ለመጨረስ ግብ ግብ ተያይዛለች። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በአንድ ወቅት በዚህችው ፍትህ ላይ በፃፉት ፅሁፍ ‹‹ዳገት ላይ ሰው ጠፋ›› ብለው ነበር። ፕሮፍ ልክ ናቸው። ዛሬ ሀገሬ ዳገቱን ጨርሶ ከገደሉ ስቦ የሚያወጣትን አላገኘችም። ምክንያቱ ደግሞ በብዙ የሚጠበቀው አንዳንዴም ገና ከታች፣ አንዳንዴም ከዳገቱ ወገብ እየቀረ ጣሯም መከራዋም ትውልድ ተሻጋሪ እየሆነ ነው፡፡ …እንዴት ያማል መሰለህ ትውልድ ተሻጋሪ መከራ? የእኔና የአንት ትውልድ ባለፉት ተከታታይ ትውልዶች ያልተከፈለ ዕዳ ተሸክሟል። የሸክማችን ግዝፈት መነሾም ይኸው ይመስለኛል። እንደቅርስ መከራን ማውረስ…
የፍትህም ጉዞ ቢሆን ዳገቱን ለመውጣት በትግል ላይ ነው። በእርግጥ መከራው እና ድካሙ በአይነትም ሆነ በአሰቃቂነት የሚጨምረው ወደፊት በተጓዝክ ቁጥር ነው። ዳገቱን ለመጨረስ በተጓዝክ ቁጥር አደጋውም እየበዛ ይሄዳል። የታዘዘውም ያልታዘዘውም የአቅሙን መሰናክል ይፈጥርብሃል። በየቀኑ መቸንከር፣ በየቀኑም ከችንካር ወርዶ ወደፊት፣ ወደፊት፣ ወደፊት… እንዴት ፈታኝ መሰለህ? እንዴት ብርክ ፈጣሪ መሰለህ? እናም የፍትህ (የነፃ ፕሬስ) ጉዞ እንዲህ እንደዋዛ ‹‹ውሾቹ ይጮኻሉ፣ ግመሉ ጉዞውን ቀጥሎአል›› ብለህ የምታልፈው እንዳይመስልህ። እውነታው ተቃራኒው ነውና፡፡ የሚናከስ እንጂ የሚጮህ ነገር አትሰማም። ስለዚህም ድንገት ልትነከስ ትችላለህ። ድንገትም ጉዞህ በአደጋ ይከበባል። ያኔም አማራጭ ከፊት ይቀመጣል። ‹‹ውጣ አትበለው ግን እንዲወጣ አድርገው›› የሚለው ለዘመናት ያገለገለው ቀመርም በስራ ላይ ይውላል። እመነኝ ይህን ቀመር ከተቀበልክ ተሸውደሀል። ከወጣ ወጣህ ነውና። ማን ነበር ‹‹ሀገሩ የሌለ የትም የለ›› ያለው? ተስፋዬ ገ/አብ ይሆን? ለነገሩ ስዬ አብርሃም ‹‹መሬትህን አትልቀቅ›› ሲሉ የጻፉ ይመስለኛል፡፡
በእርግጥ ፍትህ በአራት አመት ጉዞዋ በቂ ሊባል የሚችል ስራ ባትሰራም፣ ለሀገራችን የዴሞክራሲ ሂደት የአቅሟን ያህል አስተዋፆ ማድረጓ ሊካድ የሚችል አይደለም። ከተባዳዩ አንፃር ቁጥሩ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ለተበደሉ፣ እና ፍትህን ለተነፈጉ ድምፃቸው ሆናለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ህዝባዊ ችግሮችን፣ ሀገራዊ አጀንዳዎችን ግራና ቀኝ ፈትሻ አደባባይ አውላለች፡፡ ይህ ሲሆን መንገዱ አልጋ በአልጋ ሆኖ እንዳይመስልህ፡፡ ለነገሩ አንተ እዚችው ኢትዮጵያ ስላለህ ከአደጋ የፀዳ መንገድ ያለ ሊመስልህ እንደማይችል አውቃለሁ፡፡ እንዲያውም ይህ ሁኔታ የሚመሳሰለው ከኢህአዴግ ጉዞ ጋራ ነው፡፡
አዎ! ህወሓትን እፍኝ የማይሞሉ ሰዎች እንደ መሰረቱት ታውቃለህ። ሞኛ ሞኙ ደርግም በቆረጡ ሰዎች (ሰባትም ሆኑ አስራ ሁለት) የታሪክ ሰሪ መንፈስ እንደሚሰፍንባቸው አላወቅምና እስከውድቀቱ ዋዜማ ድረስ ‹‹እፍኝ የማይሞሉ ወንበዴዎች…›› በሚል ፕሮፓጋንዳ ጉልበቱን ጨረሰ። (ይህ የእኔ ትንተና እንዳይመስልህ። ‹‹የትውልድ ሀላፊነትን የተቀበሉ ቆራጦች አዲስ ታሪክ ሰሪ መንፈስ ይጫናቸዋል›› የሚሉት ታሪክ አዋቂ ፈላስፎች ናቸውና።) እመነኝ የህወሓትም ብርታት ከዚህ እንጂ ከሱዳን ጠንቋይ የመጣ አይደለም። ማን ያውቃል የፍትህ ጉዞስ ነፃውን ፕሬስን የት እንደሚያደርሰው? እናም ያ ቀን ለቀጣዩ ትውልድ ሲል ያጥር ዘንድ እመኛለሁ፡፡ መመኘት ብቻም አይደለም እንዲህም እላለሁ አቤቱ ታሪክ ሰሪ መንፈስ ሆይ ወዴትነህ?
የሆነ ሆኖ ከመጋረጃው ጀርባ ባለችው ኢትዮጵያ እና በኢቲቪ በምትመለከታት ኢትዮጵያ ብዙ ርቀት አለ። የኢቲቪ ኢትዮጵያ በየአመቱ 11 በመቶ የምታድግ፣ ነፃ ፕሬስ እንደ አሸን የፈላባት፣ ብሔር ብሔረሰቦች በደስታ እና በተድላ ተፋቅረው ‹‹ያምቡሌ››ን የሚጨፍሩባት፣ ፍትህ ርትዕ የነገሰባት፣ እውነትን የሚያገለግል ጋዜጠኛ የሚከበርባት፣ የስራ እድል የተትረፈረፈባት… ወዘተተርፈ ነች። እንዳልኩህ ይች ኢትዮጵያ የኢቲቪ እንጂ እኔና አንተ የምናውቃት፣ ኢህአዴግ የሚያስተዳድራት አይደለችም።
እኔና አንተ የምናውቃት፣ ከነገ-ዛሬ… እያልን የምንሰጋባት፣ ዜጐቿ ‹‹ውጡ ይህ ሀገራችሁ አይደለም›› የሚባሉባት፣ ጋዜጠኞች አሸባሪ እየተባሉ እንደ በግ ተጎትተው የሚታሰሩባት ወይም ሀገር ለቀው የሚሰደዱባት፣ ህፃናት በረሃብ እንደቅጠል የሚረግፉበት፣ ስራ እጥ የነገሰበት፣ የፍትህ ስርዓቱ ለመንግስት ጠባቂ መልዕክ የሆነበት፣ ካድሬ ያሸውን የሚያደርግባት፣ የመደራጀትና የመሰለፍ መብት የተነፈገባት፣ ሰብዓዊ መብት የሚጣስባት፣ አቤት! የሚባልበት ዳኛ የሌለባት፣… ኢትዮጵያን ነው የምናውቃት።
የፍትህ ጉዞንም በእሾህ የተከበበ ያደረገው ይህ ነው። ለዚህም ነው ደግመን ደጋግመን ‹‹ጉዞአችን ቀራኒዮ›› ድረስ ነው ያልነው። በእርግጥ ላለመሰናከል መበርታት እንደአለብን ብናውቅም ቀራኒዮ ከዚህ ምን ያህል እንደሚርቅ ግን ማናችንም አናውቅም፤ ዛሬ ምሽት እንድረስ ወይም ነገ አሊያም የሚቀጥለው አመት የሚያውቀው ገዢው ፓርቲ ብቻ ነው። ምንም አይነት እርምጃ የመውሰድ ምርጫው በገዥው ፓርቲ እጅ ነው። አዎን! ውሳኔው በእጁ ነው። ወይ ፍትህን አጥፍቶ የሚመጣውን በፀጋ መቀበል፤ አሊያም የፍትህን ጎምዛዛ ሂስ ውጦ መታረም። ከዚህ በተጨማሪም ፍትህን መዝጋት አሊያም እንድትዘጋ በስውር መዳፍ መደፍጠጥ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ላይ የመጨረሻውን ሚስማር መምታት ነው፡፡ ሚስማር ደግሞ የሚፈነቅለው ነገር ሊኖር እንደሚችል ማወቁ ጠቃሚ ነው፡፡ እስከዛው ድረስ ግን እኛ እንፅፋለን። የምንፅፈው የሀገሪቱ ህገ-መንግስት መፃፍ ትችላላችሁ ሲል መብታችንን ስላረጋገጠልን ነው። እምንከተለውም ሆነ እምንቀበለው ህገ-መንግስቱን ብቻ እንጂ የአምባገነን ባለስልጣናትን ተግሳፅ አይደለም። አንተም ይህን ልታደርግ ይገባሃል። ሀሳብህን ያለገደብ መግለፅ ትችላለህ ተብለሀልና ይህንኑ መተግበር አለብህ። ያን ጊዜም ነው ነፃነትህ በእጅህ የምትሆነው። ያንጊዜም ነው ሀገር እና ህዝብን የምታገለግለወ።
አዎን ፍትህም የምታገለግለው ሀገርንና ህዝብን እንጂ መንግስትን ወይም ተቀናቃኞቹን ባለመሆኑ እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ከመስመራችን አንድ ኢንች አንወጣም። ትላንት ጎዞአችን ቀራኒዮ ድረስ ነው ብዬሀለሁ፡፡ ዛሬም እደግመዋለው ‹‹ቀራኒዮ…ድረስ ነው››
የሆነ ሆኖ በዚህ ፅሁፍ ላይ ከከፍተኛ ባለስልጣኖች ጀምሮ እስከ ተራው ካድሬ ድረስ በሚቆጠሩ አምባገነኖች የተሰነዘሩ ዛቻ እና ማስፈራሪያዎችን፣ እንዲሁም ለቁጥር አዳጋች የሆኑ የሀሰት ክሶችን ብዘረዝር ቢያንስ ለታሪክ ይጠቅም ነበር። ሆኖም እንኳን አንድ አምድ፣ ሙሉ ጋዜጣውም አይበቃምና እናልፈዋለን፡፡ ነገር ግን እዚህች ጋ ስደርስ አንድ ነገር ትዝ ስላለኝ ላጫውትህ።
በዚሁ ዓመት በወርሃ ታህሳስ ለአንድ ሳምንት ያህል በፍትህ አዘጋጆች ላይ የደህንነት አባላት ነን ያሉ ሰዎች 24 ሰዓት ሙሉ እየተከታተሉ ያስጨንቁ ነበር። ሁኔታውም ከቀን ወደ ቀን እየከረረ እና እየበረታ ሲሄድ ሁሉም አዘጋጆች አሲምባ ገቡ። አሲምባ ግን የት ነው? ትርጓሜውስ ምን ማለት ይሆን?
መቼም በያ ትውልድ ዘመን በነበሩ ወጣቶች ልብ ውስጥ ኢህአፓ የሚባል ፓርቲ ነግሶ እንደነበረ ታስታውሰዋለህ። ደህና! ኢህአፓም ሰራዊቱን ምዕራብ ትግራይ ውስጥ ኢሮብ የሚባል ቦታ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ እንዲሰፍሩ አደረገ። ያ ተራራም አሲምባ ይባላል። ትርጓሜውም ‹‹ቀዩ ተራራ›› ማለት ነው። እናም አሲምባ ለብዙ ወጣቶች ከሞት የማምለጫ ምሽግ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። በእርግጥም እድል ቀንቶአቸው በርካታ የደርግ ኬላዎችን አልፈው አሲምባ መድረስ የቻሉ ወጣቶች ከሞት ተርፈዋል። አሲምባ ማለት በያ ትውልድ ይህ ነው።
ወደ ፍትህ አሲምባ ደግሞ እንምጣ። ከላይ እንዳልኩህ በነዛ ሰባት የመከራ ቀናት፣ ክትትሉና ጫናው አደገኛ በመሆኑ ሁለቱ የጋዜጣው አዘጋጆች ‹‹በጋራ ለቆምንለት የፕሬስ ነፃነት፣ በጋራ ዋጋ እንከፍልለታለን›› አሉና በብቸኝነት እኖርበት የነበረችውን አንድ ክፍል ቤት ተዳበሉ። ከዚህ በኋላም ክትትሉና ማስፈራሪያው በጋራ ሆነ፤ የእኛም እንቅስቃሴ ተገደበ፣ እንደጋዜጠኛ ከወዲህ ወዲያ ተሯሩጦ መስራት የማይሞከር ሆነ፡፡ ውሎአችንም ከቤት ወደቢሮ፤ ከቢሮ ወደቤት ሆነ፡፡ ይህን ሁኔታ ቅርብ ሆነው የተከታተሉ ወዳጆቻችንም ያችን በጋራ የሙጢኝ ያልናትን የኔን ቤት ‹‹አሲምባ›› ሲሉ የበረሃ ስም ሰጧት። እነሆም በግልፅ የነበረው የደህንነት ከበባው ቢነሳም (ምንአልባት በስውር ሆኖ ሊሆን ይችላል) አሲምባ ግን ዛሬም የአዘጋጆቹ መኖሪያ ቤት መሆኗን ቀጥላለች፡፡
በእርግጥ አሲምባን መኖሪያ ቤት ከማለት ‹‹ምሽግ›› ማለቱ የሚቀል ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በአሲምባ ህይወት ጉራማይሌ ነው። ከምቾት የተፋታ፣ ከደስታ የተጋባ ነውና፡፡ በምግብ በኩል በአሲምባ አብስሎ ለመብላት የሚያስችል ምንም አይነት ቁስ ስለሌለ ብዙውን ጊዜ ለእራት የሚሆነው ሙዝ በዳቦ ሲሆን፣ እንዳንዴም ጫናው ሲበረታ እንደተራቡ ማደር ይከተላል። (አሳዳጆቻችን ግን የሚያሳድዱን እራት በልተው ይሆን ወይም ሳይበሉ የሚያውቀው የመደባቸው አካል ብቻ ነው) ይህም ሆኖ በአሲምባ በጊዜ የሚተኛ የለም፡፡ ቶሎ ከተተኛ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት በኋላ ነው፡፡ አሊያም እስከ ንጋት 11 ሰዓት ይመሻል። ይህ ግን አሰልቺ አንዳይመስልህ። እንዲያውም በጣም ጣፋጭ ነው፡፡ እንዴትስ ጣፋጭ አይሆን? በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዱላ ቀረሽ ክርክር እና ውይይት እየተደረገ የሚቆይ ምሽት? እናም በአሲምባ ሲነጋ መንጋቱን የምታውቀው ከጎዳናው ላይ በሚሰማው የታክሲ ረዳቶች ተሳፋሪዎቻቸውን በሚጣሩበት ድምፅ ነው። (ስለአሲምባ ሌላ ጊዜ በስፋት እናወጋለን፡፡ አሁን ኑሮአቸውን በአሲም ባደረጉ አዘጋጆች ስለምትዘጋጀው የ‹‹ፍትህ›› ገዳለ ገደል ጉዞን ቅኝት ወደመደምደሙ እንመለስ፡፡)
አዎ! እጃችሁን ከፍትህ አንሱ ፍትህን ማሸነፍም ሆነ መጨፍለቅ አይቻልምና። በነገራችን ላይ ፍትህ ስል አዘጋጆቹን እንዳይመስላችሁ፣ መንፈሱን ነው። የመናገር፣ የመተቸት፣ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መንፈስን ማንም አይገድበውም። ማንም። የፍትህን መንፈስ (ይህን መንፈስ) ማሸነፍ ደርግን የማሸነፍ ያህል ቀላል አይደለም። ይህ ማስፈራሪያ አይደለም። ህዝብ አይሸነፍም ማለት እንጂ። መቼም ይሁን መቼ፣ የትም ይሁን የት ህዝብ ተሸንፎ አያውቅም። እናም ፍትህን አጥፍቶ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ብቻ ይኑር ማለት ትውልድን ከማጥፋት ወንጀል በምንም ሊለይ አይችልም። ሊያንስምም አይችልም። ስለዚህም በአገሪቱ ህግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዳለን ሁሉ፣ የምንሰብከውም በህገ-መንግስቱ በተረጋገጠው መብታችን ብቻ እንደሆነ እና ይህንን መብትም ሌሎችም እንዲጠቀሙበት የማበረታት ሙሉ መብት እንዳለን አውቃችሁ ልታከብሩልን ይገባል።
…የሆነ ሆኖ የፍትህ ቤተሰቦች እየከፈሉ ያለው ዋጋ ለሀገር መከፈል ካለበት አንፃር ከአየነው በጣም ጥቂቱን ነው። ምክንያቱም ለዚህች ሀገር በርካቶች የህይወት መስዋዕትነትን ከፍለው አልፈዋልና። በጎዳና ላይ በጥይት ያለቁት ወንድም እና እህቶቻችን ዛሬ እኛ እያቀነቀንን ላለው የዴሞክራሲ ስርዓት ነው። ከታሪካችን እንደተረዳነውም ካልን እልፍ አላፍት መስዋዕቶች ‹‹ሀገሬን…›› ሲሉ አልፈዋል። ለዳር ድንበር መተኪያ የሌለውን ህይወታቸውን ከፍለዋል። ለዚህም ይመስለኛል አሉላ አባነጋን የመሳሰሉ የሀገር አንድነት አቀንቃኝ ጠላቶቻችን ተሸንፈው ከሀገራችን ሲወጡ ‹‹የረገጣችሁት አፈር ላይ የወንድሞቻችን ደም ፈሶአልና ከጫማችሁ አራግፉ›› ሲሉ ያስገደዱት።
ወዳጄ! ይህን እየፃፍኩልህ ሳለ ፍትህን የከበባት አደጋ ከመቼውም ጊዜ የከፋ ሆኗል። ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እስከ አይጋ ፎረሙና አዲስ ዘመን የተሰኙ ‹‹ሎሌ›› ሚዲያዎች ከእነ ጭፍሮቻቸው የማሸማቀቅ፣ የመወንጀል፣ የማስፈራራት፣ የማስጨነቅ ዘመቻቸውን በተለያየ ግንባር ከፍተውብናል። እነዚህ ሚዲዎች ዛሬ እየፈጠሩ የሚለጥፉብንን የሀሰት ውንጀላዎች ነገ ደግሞ ማስረጃ አጠናከርንበት ሊሉ እንደሚችሉ ማንም ያውቃል። በፍትህ በኩል ግን ዛሬም እንደቀድሞ ለስደት የተዘጋጀ እግር እና አጎብዳጅ አንገት እንደሌለ ከሳሾቻችን ማወቅ ይኖርባቸዋል።
ኢትዮጵያ፤ ወደ ዴሞክራሲ የመጓዣው ጎዳና ካርታ ላይ
ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ
ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ
ባለፈው ሳምንት በሲያትል ከተማ የኢትዮጵያን ራዕይ በተመለከተ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይት፤ ክርክር፤ ለማካሄድ በተመሰረተ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ፎረም ላይ (EPFS)ላይ ተጋብዤ ተገኝቼ ነበር:: በዚህምስብሰባ ላይ በቅርቡ ሳቀርባቸው በነበሩት የኢትዮጵያን ከፈላጭ ቆራጭ ግዛት ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሽግግርን በተመለከተ ማብራሪያ እንድሰጥ ተጠይቄ ነበር፡፡ እኔ በኢትዮጵያ ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሊካሄድ ስለሚገባው የሽግግር ሁኔታ የማቀርባቸው ሃሳቦች፤ በሃገራችን በመካሄድ ላይ ያለውን ጭካኔ የተመላበት አገዛዝ፤የሰብአዊ መብት ረገጣ፤የፍትሕ እጦት፤ እስራትና ወከባን በተመለከተ ካለኝ ወገናዊነት የተነሳ የተፈጠረብኝ የግል አመለካከቴ ነው፡፡ ይህ ወገናዊነቴና ለሰብአዊ መብት ሙግት መቆም የጀመርኩበት ምክንያት በቀጥታ ትእዛዝ መለስ ዜናዊ በባዶ እጃቸው መብታቸውን ለማስከበር የወጡትን ንጹሃን 193 ኢትዮጵያዊያን ካስጨፈጨፈና 763 የሚሆኑትን ደግሞ ካስቆሰላቸው ከ2005 ጀምሮ ነው፡፡ ከ2005 በፊት ግን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የነበረኝ ትኩረቴ፤ትምህርታዊ፤ እንዲሁም ስለኢትዮጵያ ጉዳይ በሚያነሳ አንድ ምሑራዊ መጽሔት ላይ መስራትና በኤዲቶሪያል በኩልም ሕትመቱን ማገዝ ነበር፡፡ የ2005ቱ ጭፍጨፋ በሁዋላ ፤ጭፍጨፋው አልተፈጸመም ብዬ ዝም የማለት ምርጫ ነበረኝ፤ በደረሰው አስከፊና ዘግናኝ ሁኔታ ለራሴ በራሴ ተብሰልስዬና ውስጤ ቆስሎ ነገሩን ችላ የማለት አማራጭም ነበረኝ፡፡ እነዚህ በግፍ የሞቱትን ንጹሃን ጉዳይ ግፈኞቹና ነፍሰ ገዳዮች ስልጣናቸውን ለግፍ መፈጠሚያ የሚያውሉትን አረመኔዎች ሊሞግትና ጥብቅናሊቆም የሚወስን አካል ይፈጠራል፤ በማለት ዝም ማለት፤ እችል ነበር፤ አለያም ስልጣናቸውን አላግባብ ለግፍ የሚያውሉትን ፈላጭ ቆራጮች በተመለከተ ቆራጥ ሆኜ ለተበደሉት ጥብቅና ለመቆምና ድምጸቸውን ለማሰማት የመወሰን ግዴታ እንዳለኝ ተገነዘብኩ፤ ምርጫዬም የሰብአዊ መብትን መሟገትና ለዚህም ጥብቅና መቆምን ሆነ፡፡
ዴሞክራሲ (ቢያንስ በጥቅል ትርጉሙ) በሕዝብተቀባይነት ያለው መንግስታዊ ቅርጽ ነው፡፡ የነጻነትን ምንነትne ያላገናዘበ፤(ማለትም በነጻ ማህበራትን ማደራጀትን፤ሃሳብን በነጻ መግለጽን፤ የነጻውንፕሬስ አለማክበር ባዶ ቀፎ ነው የሚሆነው፡፡ ዴሞክራሲ ሲባልም ሰብአዊ መብትንና ፍትህን ተጠያቂነትን ማክበርና፤የሕግ የበላይነትን መጠበቅ ፤ነጻ የፍትህስርአት፤ግልጽነት፤ተፎካካሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና የሲቪል ማሕበረሰቡን ያካተተ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫን፤ማካተት አለበት ፡፡የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ድንጋጌ ቁ. 21(3)ዴሞክራሲንና ሰብአዊ መብትን ያዋህዳቸዋል፡፡ ለማንኛውም የመንግስት ስልጣን መሰረቱ የሕዝቦች ፈቃደኝነት በመሆኑ ይህም ሕዝባዊ ፈቃደኝነት በማንኛውም ጊዜ ሊከበር የግድ ነውናበፍትሃዊ ምርጫ ወቅትም ሊተገበር ይገባል ፤ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ትርጉምና ጠቀሜታ ያለውን የዴሞክራሲ መብቶች ያካተተ ጥላ ነውና የዴሞክራሲን ተግባራዊነት በትክክለኛው መንገድላይ ያስኬደዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሞካሄደውን ለሰብአዊ መብት ትግል ለዴሞክራሲና ለመሰል ትገሎች የሚካሄድ ትግል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ለሚደረገው ሽግግር የእኔነቴ ስሜት የተነሳሳው፤ ምክንያቱም ሽግግሩ ከተሳካ፤ሰብአዊ መብት ይከበራል፤ ይረጋገጣል ይጠበቃልም ብዬ አምናለሁ፡፡
በዴሞክራሲው ጎዳና ላይ ያለው ድልድይ
ከጭቆና አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ጎዳና እንደ ነጻነት፤የሰብአዊ መብት መከበር ብርሃን (የዴሞክራሲ) ተምሳሌታዊ ጉዞ ልንወስደው እንችላለን፡፡በዚህ ጎዳና ላይ ሕዝቦችም ሆኑ የማሕበረ ሰቡአባላት በሁሉም አቅጣጫ የሚንቀሳቀሱት፡፡የፈላጭ ቆራጭ ስርአትም ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚቀየረው ፡ በዚህ ድልድይ ላይ ነው:: የሕዝቦችም ሆነ የሕብረተሰቡ፤ ትልቅምሆኑ አናሳዎች የሚፈጠሩትና የሚጠሩትና የሚጠፉትም፡፡በድልድዩ ላይ የሚከናወነው ሽግግር ስርአትን የጠበቀ፤ምክንያታዊ ሆኖ በዘዴ የሚመራ ከሆነ ዴሞክራሲ በእውን ይገነባል፡፡ ድልድዩየተተረማመስ፤መግባባት የጎደለው፤ አፍራሽነት፤ጉልበትን መሰረት ያደረገ ከሆነ ግን ድልድዩን መሻገር ዘበት ሆኖ ወደ ተጠላው ፈላጭ ቆራጭ ስርአት መልስ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ጊዜው ሲቃረብና የፈላጭቆራጭነትና የዴሞክራሲያዊ ስርአትን የሚያስተላልፈው ሰአት ላይ ስንደርስ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለው ጉዳይ ነው የሚያሳስበኝ፡፡
በበርካታ ምክንያቶች የተነሳ ኢትዮጵያ ወደዚያ የዴሞክራሲ አስተዳደር ድልድይ በተፋጠነ መልኩ በመጓዝ ላይ ነች ብዬ አምናለሁ፡፡ምንም እንኳን ፈላጭ ቆራጭ ገዢው 99.6 በመቶ ምርጫውንአሸንፌያለሁ በማለት ዜማ የለሽ የሃሰት ከበሮውን ቢደልቅና የመርገጫ ማህተም የሆነውም ፓርላማ ቢያጸድቅለትም፤ ገዢው ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት አንዳችም ሕዝባዊ ይሁንታና አመኔታ የሌለውነው፡፡ ኤኮኖሚው ተፈረካክሷል፤በአዲስ አበባ የሚገኘው አክሴስ ካፒታል ሼር ኩባንያ የተባለው ተመራማሪ ድርጅት እንዳለው፤በ2011 40.6 የዋጋ ግሽበት በማስመዝገብ ኢትዮጵያ በዓለም ሁለተኛውን የዝቅዝቅ ደረጃ ይዛለች ብሎ ዘግቧል፡፡የዓለም ባንክም እንደጠቆመው፤ ኢትዮጵያ በርካታ ባለባት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ሳቢያ በበርካታ ችግሮች ተወጥራለች፡፡የድህነት ቅነሳውም በዚሁግሽበት ታግዷል፡፡በጣም የተዋከበና ያልተረጋገጠ የገንዘብ ፖሊሲ፤ እድገትን እንደግመል ሽንት ወደኋላ ከመሳቡም አልፎ የማይክሮኤኮኖሚውን መረጋጋት ያዋዥቀዋል፡፡የኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪውእድገት ማዝገም በብዙ ሰበቦች ወደ አዘቀዘቀ የአምራጭነት ደራጃ ያወርደዋል፡፡
እናም ውጡቱ የማይሰተካከል የንግድ ኪሳራ ነው፡፡ በገዢው መንግስት ስረአት አልበኝነትና በራሱ በመሰነጣጠቁ የተነሳ ተቃውሞ የበዛበት ሆኗል፡፡ በርካታ ዜጎችን ከመኖርያ መንደራቸው ማፈናቀል፤ብዙዎች‹‹ የዘር፤ የጎሳ ማጥፋት››የሚሉት በግልጽ ገዢውን ስርአት በመቃወምና በጎሪጥ ወደመመልከቱ አድረሷቸዋል፡፡በገዢው ፈላጭ ቆራጭ መንግሥትና በደጋፊዎቹ በሌላ ጎኑ ደሞ ብዙሃኑ ሆነውበመሃላቸው በእጅጉ የናረ ጥላቻ እየታየ ነው፡፡ ገዢው መንግስት ያፈጠጠውንና ሕብረተሰቡን ለችጋርና ለመረረ ኑሮ የዳረገውን፤ ማህበረሰብአዊ፤ ኤኮኖሚያዊና ፖቲካዊ፤ ዝብርቅርቅ ችግሮች ለመፍታትአዳዲስ ዘዴዎችን የመጠቀም ፈቃደኝነትም ሆነ መንገዱ ስለጠፋበት ሙሉ በሙሉ ጨልሞበት አጉል የሕዝብ ግንኙነት ፕሮፓጋንዳ መርጦ ግድብ መገንባት፤ኢንቬስትመንትን ማበረታታና ማጎልበት የሚልችግሮችን የመሸፈኛ ጭንብል ለማጥለቅ መመኮሩ በሃገር ውስጥና ከውጭውም የበለጠ ተቃውሞ እያስከተለበት ነው፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎችም የፈላጭ ቆራጩ መንግሥት መበስበስ በተደጋጋሚ ታየቷል፡፡የዚህ መሰረቱ የተናጠ አገዛዝ አወዳደቁ በውስጡ ከሚፈጠር እምቢተኛነት ይሁን፤ሕዝባዊ እምቢታ ወይም በሌላ መንገድ ይሀን አሁን መተንበይ ያስቸግራል፡፡፡
በቅርብ ርቀት ያለው ድልድይ
የሰው ልጅ ታሪክ ከመነሻው አንስቶ ከጭቆናና ከፈላጭ ቆራጭ አረመኔያዊ አገዛዝ ለመላቀቅ የሚደረግ የትግል ታሪክ ነው የሚለውን ፍልስፍናዊ ዓላማ የምንቀበል ከሆነ፤ በተፈጥሮ የሰው ልጅ ፍላጎትምነጻነትን በመቀዳጀት ጭቆናንና ተገዢነትን በማስወገድ ላለመመለስ መቁረጥ ነው፡፡ ጨቋኞችና ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች፤በሙስናና እና በጉልበት ነጻነትን ማፈን እንደሚችሉ በማመን እራሳቸውን ያሞኛሉ፡፡ሆኖም ማቆም የማይቻለው የነጻነት ሂደት ግን በነዚህ ግፈኞች ላይ የራሱን ታሪካዊ ሕግጋት ያሳርፋል፡፡
የፈላጭ ቆራጭና የጨቋኞች ቀዳሚ ሕግጋትም የእነሱ መውደቅ አለመቅረቱ ነው፡፡ጋንዲ ስለዚህ ጉዳይ ‹‹በታሪክ ሂደት ሁሉ ፈላጭ ቆራጮችና ነፍሰ ገዳዮች ነበሩ፤ጊዜያዊም ቢሆንየማይደፈሩ መስለው ይታያሉ፤ በመጨረሻው ግን መውደቃቸው የማይቀር ነው፡፡ይህንን ምንጊዜም በህሊናችሁ አስቡት›› ባለፈው ዓመት ብቻ ፈላጭ ቆራጭ አረመኔ ገዢዎች በቱኒዚያ፤በሊቢያ፤በግብጽእና በየመን እንደቅጠል ሲረግፉ መስክረናል፡፡ በነዚህ ሃገሮች በተዘጋጁና ለግፈኛ ገዢዎች መኖር ብቻ በቆሙ ሰላዮች፤ የጦር ወታደሮችና ፖሊሶች የሕዝቡ የነጻነትና ሰብአዊ ክብር ፍላጎት ጨርሶ ሊገታአልተቻለም፡፡ ሁለተኛው የታሪክ ህግ ደግሞ እነዚህ ከ ስልጣን የወደቁ ፈላጭ ቀራጭ አረመኔዎች ከውድቀታቸው በኋላ ዘወትር ብጥብጥን አለመግባባትን፤ግጭትን ነው ትተውየሚያልፉት፡፡ ይህም ‹‹በአረቦቹ መነሳሳት›› ወቅት የታየ ነው፡፡ሶስተኛው ታሪካዊ ህግ ደግሞ የፈላጭ ቆራጮች መውደቅ የሚያስከትለው ዳፋ ለመገመት አስቸጋሪ መሆን ነው፡፡በእርግጠኝነት ግን የፈላጭ ቆራጮች መውደቅ የዴሞክራሲን መምጣት አያረጋግጥም፡፡ይልቁንስ በፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች መውደቅ ሌላ ፈላጭ ቆራጭ ገዢ መነሳትን ነው የሚያስከትለው፤ ምክንያቱም እነዚያ ፈላጭ ቆራጮችን ከዙፋናቸው ያስወገዱት፤ አላማቸው እራሳቸውን በባዶውየዙፋን መንበር ላይ በማስቀመጥ እንዳለፉት ለመግዛት በማቀዳቸው ነው፡፡ ማለትም ‹‹ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም›› እንደሚባለው ያለ ነው፡፡ ወይም ጠርሙሱ ተለዋወጠ እንጂ ወይኑየድሮው ነው እንደማለት፡፡ አራተኛው ሕግ ደግሞ አንዳንድ ጭክ ብለው ሙጢኝ ሥልጣኔ አምባገነኖች እስከመጨረሻው በመቸክ ሥልጣናቸውን ለማቆየት ሲብገታገቱ ነው::
በዴሞክራሲ መሸጋገርያው ድልድይ ላይ ሥልጣንን በማሳደድ ላይ ባሉት ግለሰቦችና ቡድኖች መሃልና እንዲሁም ጭቆናና ግፍ በሰለቻቸው የሕብረተሰብ አባላትና በስልጣን አንለቅም ባዮች ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች መሃል የግጭት መፈጠር ይከሰታል፡፡በዚህ ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ በሚወስደው የሽግግር ድልድይ ላይ የፖለቲካ ስልጣንን ለመጥለፍ አመቺው ሁኔታ ይፈጠርና፤በዴሞክራሲ ስም የፈላጭ ቆራጭነትን ሥላጣን መልሶ ለመገንባት አጋጣሚውን ይጠቀሙበታል፡፡ይህን በሚገባ የሚገልጽ አባባል በኢትዮጵያችን አለ ‹‹ግርግር ለሌባ ይመቻል›› ሁሉም አይነት የሂደቱ ተካፋዮች ከያሉበት ወደ ዴሞክራሲው መሸጋገርያ ድልድይ ይሰባሰባሉ፡፡ ሁሉም አይነት ተንኮል፤የሥልጣን ሽሚያ፤ችግሮች ሁሉ ይመጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ እንደታየው የታሪክ እውነታ የሚከተለውን ያስገነዝበናል፡፡ ሊሆን የሚችለውም ይህን የመሸጋገርያ ድልድዩን ዋነኛ የተባሉት የውጭ ሃይሎች የሽግግሩን ወቅትና ሽግግሩን ራሱን ሊቆጣጠሩትና ሊመሩት ፈቃደኛነታቸውን በማሳየት ራሳቸውን እንደሸምጋይ ያቀርባሉ፡፡ በዚህም ራሳቸው ያስቀመጧቸውን ምልምሎችቸውን ቦታ ለማስያዝ የሽግግር ድራማቸውን በማቅረብ ሕዝቡም የፈላጭ ቆራጮች አገዛዝ ሰልችቶት አዲስ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ናፍቋልና እነዚህ ሽማገሌ ሆነው የቀረቡት አሸማጋዮች በሽግግሩ አውቶቡስ መሪው መቀመጫ ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ተሳፋሪዎቹንም ወደፈለጉት አቅጣጫ ያጓጉዟቸዋል፡፡
የጦሩ ክፍል (ቢያንስ በአመራር ላይ ያሉት) በሽግግሩ ወቅትና በሃሰት ወርቀዘቦ በተጠቀለለ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ተስፋ፤ ሕግና ስርአትን ማስጠበቅ ሰላምን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው በሚል ሽፋን፤የሕዝቡን አመኔታ ለማግኘትና የእርዳታ ሰጪዎችን ችሮታ ለመቧገት ሲሉ ተጠያቂነትን፤ ሙስናን መከላከልን፤ሰብአዊ መብትን ማስከበርን፤ ሰበብ በማድረግ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ ይጥራሉ፡፡በዚህም ለሕብረተሰቡ ከሽግግር ይልቅ የወታደራዊ አገዛዝን በሲቪሉ ሕዝብ ላይ ይጭናሉ፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችም ተሰባስበው ለስልጣን ሽኩቻ ይዘጋጃሉ፡፡ አንገታቸውን ደፍተው የነበሩ የውስጥ ሃይሎችም ከጨቋኝ ገዢዎች ስርአት ግፍና መከራ ከተላቀቁ በኋላ የስልጣን ተጋሪነታቸውን ለማረጋገጥ በድርድሩ ጠረጴዛ ላይ ይሰየማሉ፡፡ አዳዲስ ቡድኖችም በመሰባሰብ ተደራጅተው፤የስልጣን ተጋሪነታቸውን ያሳውቃሉ፡፡ የየክልሉም ሰዎች ለራሳቸው የሚመቻቸውን ለማረጋገጥ በሽግግሩ ወቅት ሚና እንዲኖራቸው ያደርጋሉ፡፡የወደቀው ስርአትም ርዝራዦች እራሳቸውን በማደራጀት አለያም ከአለውና ፍላጎታቸውን ከሚጠብቅላቸው ቡድን ጋር በመቀላቀል ራሳቸውን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
እያንዳንዱ ቡድን ለስልጣንና ለማግባባት ሲጋልብ በዚህ የስልጣን ስርቆት ውስ ይበልጡን ተጎጂ የሚሆነው ሕብረተሰቡ ነው፡፡ ወደ ዘር፤ ቋንቋ፤ ሃይሞኖት እና ጎጥ ጎራ ያስገቡታል፡፡ የቆየ ታሪክ እየተነሳ ለክስ ይቀርባል፤ የመገንጠል ማስፈራራትም ይከሰታል፤ክስና ቁርሾ ይነሳና የህብረተሰቡን አስተሳሰብ ያስጨንቀዋል፡፡በመጨረሻም ሕብረተሰቡ የግራ መጋባት፤እሮሮ ድህነት፤ችጋር፤መከራና የተሰበረ ልብ ሻንጣ ተሸካሚ ሆኖ ይቀራል፡፡
በግርግሩ የሽግግር ድልድይ በእርግጠኝነት አንድ ነገር ያጋጥማል፡፡የስልጣን ክፍተት፡፡በዚህ የስልጣን ክፍተትና ግርግር መሃል ነው ብልጣ ብልጦችና በደንብ የተደራጁ ቡድኖችና ግለሰቦች በሚገባ የተነደፈና የተዘጋጀ እቅዳቸውን በማቅረብና በመጠቀም፤የስልጣኑ ኮርቻ ላይ በመፈናጠጥ ከፈላጭ ቆራጭ ስርአት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ሽግግር የሚያጨናግፉት፡፡
ውድቀትን ማቀድ ለመውደቅ መዘጋጀት ነው
በኢትዮጵያ ለሚከሰተው ፤ለማይቀረው፤ለማይቆመው፤ ለማይታለፈው ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ሽግግር በሚገባ ማቀድ ያስፈልገናል፡፡የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በኢትዮጵያ ያልቅለታል፡፡ዋናው ቁም ነገር የዴሞክራሲ ትንሳኤ መቼ ነው ነው፡፡ ጥያቄውም መቼና ምን መሳይ የሚለው ነው፡፡አሁንም አንድ ሌላ ኢትዮጵያዊ አባባል ሃሳቤን ይግለጽልኝ ‹‹ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ›› እንዳይሆንብን ከአሁኑ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ችግር የለሽ ሽግግር አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ፈላጭ ቆራጩ ስርአት ሲወድቅ ሳይሆን አስቀድመን ልንዘጋጅና መሰረታዊ የሆኑትን ቅድመ ሁኔታዎች በመነጋገር ማዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ቢያንስ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከአሁኑ ውይይቱ ሊጀመር ይገባል፡፡
1) በሽግግሩ ወቅት የባለመብቶችን አስተሳሰብና አመለካከት በማዳበር ሊያጋጥምና በሸረኞች ሊጫር የሚችለውን ግርግርና አላስፈላጊ ረብሻ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ንቃት ማስገኘት፡፡
2) የሽግግሩን መምጣት አይቀሬነት በማወቅና ተከታዩን ሁኔታ በመፍራት ቀድመው የዘር፤የሃይማኖት፤የጎሳ፤ግጭት ለመፍጠር የሚደረገውን ደባ በተቻለ ለማስቀረትና ሰላማዊ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል ዘዴ መቀየስ፡፡
3) የሲቪል ማሕበረሰቡን ተቋሞች ሕዝባዊ ግንኙነቶች እንዲካሄዱ የማድረግ ጥረታቸውን አዳብረው በሽግግሩ ወቅት ተግባራዊ ማደረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ሽግግር አስፈላጊውን ከወዲሁ በማቀድ አለመንቀሳቀስ ሂደቱን ከማኮላሸት ጋር ተመሳሳይ ከመሆንም አልፎ የዴሞክራሲ ስርአትን ማምጣት ሳይሆን ሌላ ፈላጭ ቆራጭ መንግስት እንዲተካ ማመቻቸት ይሆናል፡፡ ከቅርብ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች መማር ይገባናል፡፡ሊቢያውያን አሰቀድመው ስለሽግግር ባለማሰባቸው የተነሳ፤ በውጭ ሰዎች አደራዳሪነት አንድነት ፈጥረው በአጋጣሚው በመጠቀም ጋዳፊን ለማውረድና ለማዋረድ በቅተዋል፡፡ዛሬም ቢሆን ሊቢያ በጎሳ ግጭት ወከባ ውስጥ ገብታ፤በከረረ የፖለቲካ፤የአካባቢ ልዩነት ባስከተለው የመረረ ቁርሾ ውስጥ ናት፡፡ ቤን አሊ አስቀድሞ ጥሎ በመፈርጠጡና ወታደራዊ ተቋሙም ከሽግግር ሂደቱ በመገለሉ፤ ቱኒዝያ በነዚህ ሁለት ምክንያቶች የተሻለ ሁኔታ አላት፡፡ ግብጽ ደግሞ በሽግግሩ ድልድይ ውስጥ መውጫ ያጣች ትመስላለች፡፡ወጣት የዴሞክራሲ ፋና ወጊ ወጣቶች ሥልጣንን በብር ሰሃን አስጊጠው ለወታደሩ ካስረከቡ በኋላ ሙባረክን ለዓመታት ሲጠብቅና ሲከላከልለት የነበረው ወታደራዊ ሃይል ስልጣኑን ከተረከበ በኋላ ወጣቱ የትግሉ ባለቤት ወደ ጎን ተገፍቷል፡፡ የዚህ ትግል ፋና ወጊ የነበረውም የሲቪሉ ማህበረሰብ ተቋማትም በወታደራዊው ሃይል ገሸሽ ተደርገው ለጭቆና በድጋሚ ተዳርገዋል፡፡ ብዙ ልውውጦች በተከናወኑ ቁጥር ለውጡ ይቀርና እንደነበር መሆንን ያስከትላል፡፡
የግብጹ ፕሬዜዳንታዊ ምርጫ ለመጪው ሜይ ታቅዶ ሳለ፤የግብጽ አስተዳደራዊ ካውንስል ችሎት አዲሱን የግብጽ ሕገመንግስት ከጨቋኙ ስርአት መውደቅ በኋላ የሚያረቁትን 100 አባላት ያሉትን ሕጋዊ ኮንግሬስ አገደ፡፡ ይህም እገዳ በተለያዩ የእምነት አባላት መሃል እና ሃገሪቱን በመምራት ላይ ያለውን ወታደራዊ ካወንስል ሁሉንም ወደ መደናገጥና ውጥረት ጨምሯል፡፡ ሕገመንግስት አልባ በሆነ ወይም በቀድሞው ሕገመንግስት የሚመራ ፕሬዜዳንት መምረጥ ከፈረሱ ጋሪውን እንደማስቀደም ያህል ነው፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ ግን አብላጫውን ቁጥር በያዙት በሙስሊም ብራዘርሁድ የነጻነትና የፍትህ ፓርቲ እና የሳላፊስት ኑር (በፓርላማ አብላጫውን መቀመጫ የያዘው) ፓርቲ የሚመራው የዚህ ሕገ መንግስት አርቃቂ ካውንስል የመረረ ችግር አለበት፡፡ ሃይማኖታዊ አባለት የእስልምናና የክርስቲያን ተወካዮችን ጨምሮ በግድግድው ላይ በእጅ የተጻፈውን በማንበብ ከካውንስሉ ለቀቁ፡፡ ሴቶችና የሲቪል ማህበረሰቡ አባላት ውክልናቸው በጣም አናሳ ነው፡፡ይህንን የአንድን ሀገር መተዳደርያ የሆነውን ሕገመንግሥት ለማርቀቅ ከተሰየሙት መሃል ጥቂቶች ናቸው የሕግ ችሎታና እውቀት ያላቸው፡፡ከባለጉዳዮቹ ውክልና ሚዛን ማጣት ባሻገር፤ አንዳንድ ሕገመንግስታዊ ችግር የሚያስከትሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ዋነኛው አሳሳቢ ነጥብ፤የእስልምና ሕግ (ሻርያ) በሕገመንግሥቱ ውስጥ የተሰጠው ሚና ነው፡፡የሴቶችን መብት፤የአናሳ ሃይማኖታዊ ተቋማት መብት፤ የግለሰብ መብትንና የሌሎችንም የማህበረሰብ አባላት መብት ጥበቃ ባላሟላ ረቂቅ፤ ሚዛናዊ የመብት ጥበቃ እንዴት ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህ ሁሉ ግርግርና ውጥንቅጥ ሁኔታ ውስጥ አንድ ሰው ብቻ በፖለቲካው ሜዳ ላይ ገዝፎ ይታያል፡፡ ከወታደራዊው ተቋም በተሰጠው ይሁንታ መሰረት የቀድሞው የግብጽ ምክትል ፕሬዜዳንትና የደህንነት ሹም፤ለፕሬዜዳንታዊ ምርጫ ተዘጋጅቷል፡፡ይህ ግለሰብ ከምር ምርጫውን ካሸነፈ ለዴሞክራሲ ስርአትና ለነጻነት ብዙ ሕይወት የተከፈለበትና ሕዝብ መከራ ስቃዩን የበላለት የግብጽ የዴሞክራሲ ጨዋታ ፍጻሜ ይሆናል፡፡የግብጽ ግስጋሴ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአትም መሆኑ ቀርቶ፤ ወደ ግብጽ የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ስርአት ምለስት ይሆንል፡፡ ስለዚህም፤ነገሮች በተደጋጋሚ በተለዋወጡ ቁጥር እነበሩበት ቦታ ይመለሳሉ፡፡ ከግብጽ የዴሞክራሲያው ስርአት ሽግግር ኢትዮጵያ በእጅጉ ብዙ ልትማር ትችላለች፡፡
ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርአት የሚደረገውን የሽግግር ውይይት ማን ይመራዋል?
የኖረው አስተሳሰብ ከፈላጭ ቆራጭ የግፍ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለሚደረግ ሽግግር ውይይቱ ለምሁራን–ለፖለቲካ ሰዎች፤ ለፓርቲ መሪዎች፤ለቢሮክራቶች፤ለምሁራ እና ለሌሎችም ተቋማት መሪዎች ሊተው ተገቢ ነው ይላል፡፡ የአካሄዱን መንገድ ቅያስና ተግባራዊ እቅዱን በሚገባ ለማዳበር ጥሩ ጠቃሚና ጉልህ ሃሳብ ስላላቸው ለዴሞክሲያዊ ስርአት የሚደረገውን ሽግግር ውጤታማ ያደረጉታል፤ በዚህም ውስጥ ሁሉም የማህበረ ሰቡ አባላት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤የሲቪሉን ማህበረሰብ ተቋማት፤ሴቶችና ወጣቶች ሊካተቱበት የግድ ነው፡፡ እንደእውነቱ ከሆነም የዚህ ሽግግር ሂደት በሲቪሉ ማህበረሰብ ተቋማት፤ሴቶችና ወጣቶች መሪነት ቢካሄድ ውጤታማነቱ የበለጠ ፍሬያማ እንደሚሆን ይታመናል፡፡በሽግግር ወቅት እነዚህ ስብስቦች በርካታውን የማህበረሰቡን አባላት ሊያሰልፉ ስለሚችሉ ለሚገኘውም ውጤት ፍሬያማነት ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ድምጻቸው የታፈነውን፤ምሰኪኖች፤ጭቁን የማሕበረሰቡን ተገፉትን ድምፅ ስለሚያሰሙላቸው ተሳትፎውን የሁሉም የማድረግ ሃይል አላቸው፡፡
የወደፊቱ የራሱ ስለሆነ ወጣቱ እጅጉን አስፈላጊና ጠቃሚም ነው፡፡ጆርጅ አይቴ እንደሚለው በአፍሪካ ሁለት ትውልዶች አሉ፡፡አንዱ የአነር ትውልድ ሲሆን ሌላው ደሞ የጉማሬ ትውልድ ነው፡፡አነሮች እውቀት ዘመናዊነት ፈላጊ ና ለሚከሰቱ ችግሮች መውጫ መንገድ ይፈጥራል፡፡ጉማሬ ደሞ ሌሎችን ይወቅሳል፤ ይኮንናል፤ ይረግማል፤ምጽዋት ጠባቂ ስለሆነም አህጉራችንን ወደመቀመቅ ይወስዳታል፡፡ አዲሱ የአፍሪካ ፍጡርና ስለ ሙስና አርቲ ቡርቲ የማያወራው አነሩ ወጣት ነው፡፡ተጠያቂነትና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ምን እንደሆነ ጠንቅቆ የተረዳ ነው፡፡ መንግሽት ምንም እንዲያደርግላቸው አይጠብቁም፡፡የአፍሪካ ምጽአትና ትንሳኤም በነዚህ አነር የአፍሪካ ልጆች ጫንቃ ላይ ነው፡፡‹‹የኢትዮጵያ መዳንና ከክፉ በሽታ መላቀቅም በነዚህ አነሮች መዳፍ ውስጥ ያለ ነው፡፡ ታሪክ እንደሚመሰክረው እስከዛሬ ድረስ ተገልለው፤ ተገፍተው፤ተረስተው፤ተንቀው የነበሩት ሴቶችም በዚህ ሂደት ውስጥ በቂ ሚና ሊኖራቸው አስፈላጊ ነው፡፡ የጾታ እኩልነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ እውነተኛውና ትክክለኛው የዴሞክራሲ ስርአት ጨርሶ ሊፈጠር አይችልም፤ በግልጽ የሚታየው የኢትዮጵያ ሁኔታም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው፡፡ በግልጽ እንደሚታወቀውና ሊካድም የማይችለው፤ሴቶች በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የሶሽዮ ካልቸርና የኤኮኖሚ ጭቆና ሰለባ ከመሆናቸውም አልፎ በግላቸው ለልማት ለመንቀሳቀስ፤ ለትምህርት፤በሥራ ለመሰማራት ከወንዶች እጅጉን ያነሰ እድል ነው ያላቸው፡፡ በሽግግሩ ሂደት ንግግር ላይ የሴቶች መሳተፍ ጠቀሜታው የራሳቸውን ልዩ አመለካከትና ግንዛቤ ይዘው ስለሚቀርቡ ነው፡፡ ልዩ የመሪነት ችሎታ ስላላቸው ለዴሞክራሲው ሽግግርና ለአስተዳደሩ የሚበጅ ዘዴ ይዘው ይቀርባሉ፡፡ከዚያም አልፎ ከወንዶች ይበልጥ ታማኝ፤ብልህ፤ተግባቢና ታማኝ ናቸው፡፡ሩሩህ በመሆናቸውና፤ከወንዶች በተሸለ መደራደር ስለሚችሉ፤መቻቻል ስለሚያውቁበትም አስፈላጊነታቸው አያጠያይቅም፡፡በኢትዮጵያ ጥቂቶች ብቻ ማንነታቸውንና ችሎታቸውን ለማስመስከር እድል ያገኙ በመሆናቸው በትክክል ስለሴቶች ችሎታና ብቃት ማወቅ አንችልም፡፡ ስለዚህም በኢትዮጵያ በሚካሄደው የዴሞክራሲያዊ ስርአት ሽግግር ውስጥ በሚካሄደው የመወያያ መድረክ ላይ ሴቶች በቂ ሚና ሊኖራቸው ተገቢ ነው፡፡
ውይይቱ የዴሞክራሲ ስርአቱን ራዕይ መዳረሻ በማድረግ ወደ ብሔራዊ መግባባት ሊያመራ ስለሚችል፤ይሀ ደግሞ በኔ ግምት ሁልጊዜም ሕዝብን ወደሚያከብርና የሚፈራ መንግስት መመስረት፤የፖለቲካ ስርአቱም ሕዝቡ ጨርሶ የማይፈራውን ስርአት የሚያመጣ—የኢትዮጵያን ሕዝቦችም ወደ መግባባቱ የሚያቀራርብ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ውይይቱ በሕዝባዊ አዳራሾች፤ በጎዳናዎች፤መፓርኮችና በሕዝባዊ መናፈሻዎች፤ በመንደሮች፤ በገጠር መኖርያዎች፤ በየመንደሩ፤በጋዜጣዎች ላይ፤ በቢሮዎች፤በስብሰባ አዳራሾች፤በስታዲዩሞች፤በወጣቶችና በሴቶች ማእከላት፤በንግድና በገበሬ ማህበራት፤በት/ቤቶችና በዩዮ፤ቴሌቪዢን፤በድህረ ገጾች፤በፌስቡክ፤በቲዊተር፤በዩቲዩብ፤በስካይፔ፤በኢሜይልና በሁሉም አቅጣጫ ሊጀመርም ሊቀጥልም ይገባል፡፡
Subscribe to:
Posts (Atom)