Wednesday, April 18, 2012

የመለስ የማጥቃት ስትራቴጂ


ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመምህራን ጥያቄ ላይ የዘገየ መልስ ለመስጠት ወደ ፓርላማው ጎራ ብለው ነበር። ይህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመምህራኑ የተሰነዘረው የመልስ ምት አላማውን እና ግቡን የሳተ ነበር። እንደ ሌሎቹ ሃገራት ቢያድለን እና መምህራኑ ጥያቄ ባነሱበት ወቅት አፋጣኝ ምላሽ ቢሰጡ ኖሮ የማጥቃት ስትራቴጂያቸው ላይ ጥያቄ ባላነሳን። የሆነ ሆኖ በመምህራኑ የተነሳው ጥያቄ ላይ መድፋቸውን ተኩሰው መምህራኑን አቁስለው በጉልበት ካንበረከኩ በሁዋላ መድረኩ ላይ ወጥተው ማቅራራታቸው ትዝብት ውስጥ ይከታቸዋል እንጂ በጀ አያስብላቸውም።
ስለ አቶ መለስ ባሰብኩ ቁጥር ሁሌም የሚገርመኝ ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የቁጥር ስሌታቸው ነው። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በተመለከተ 11 ነጥብ ላይ ተንጠልጥለዋል። በምርጫው ደግሞ 99.6 ሲሉ ክችች ብለዋል። አሁን ደግሞ በብዙሃን መምህራን የተነሳውን ጉዳይ ከአንድ ፐርሰንት ያነሱ በማለት ህዝባቸውን ሊያምታቱ ሞክረዋል። በነገራችን ላይ አቶ መለስ የስራ ማቆም አድማ ያደረጉት መምህራን ከ500 የሚበልጡ አይደሉም ሲሉ ቢሳለቁም ቁም ነገሩ 500 ወይም አምስት መሆኑ ሳይሆን ጥያቄው መነሳቱ በራሱ ሊያስደነግጣቸው በተገባ። የስመ ጥሩው ኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤት መምህራን በሙሉ ጥያቄ ማንሳታቸው ብቻ ትልቅ ሃገራዊ ጉዳይ በሆነም ነበር። በመለስ የቁጥር ስሌት አምስት ሆነ አምስት መቶ ወይም 99.9 እያሉ እውነታው ላይ ከመዘባበት የመምህራኖቹ ጥያቄ ምን ነበር ብሎ በሰከነ ልቦና ማድመጥ በተገባቸው ነበር።
 የአቶ መለስ ሌላኛው ባህሪ የእኔ ተቀናቃኝ ነው ብለው ያሰቡትን ወይም ጥያቄ ያነሳባቸውን ሁሉ ከኦነግ፣ ግንቦት 7 እና ከሻእቢያ ጋር የመደመር አባዜያቸው ነው። እነዚህ ድርጅቶች በተኙበት ሳይቀር የሚያቃዥዋቸው አስመስሎባቸዋል። ምንም እንኳን “መለስ ከልጅነት እስከ እውቀት”  በሚለው መጽሃፍ ላይ “ሁሌም ከእንቅልፍ የሚያባንነኝ ስጋት አለ ይቺ ታላቅ ሃገር ከአንድ ሺህ አመት በፊት ታላቅ የነበረች ሃገር አስከፊ አዘቅት ውስጥ ገብታ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ የተራቡባት እና የሞቱባት ሃገር ምናልባት በመፈረካከስ ላይ ትሆን? የሚል ፍርሃት ከእንቅልፌ ይቀሰቅሰኛል” ቢሉንም ቅሉ አሸባሪ ሲሉ የሰየሟቸው አባናኝ ሆነውባቸዋል።
በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ግብ የለሸ መሆን የሚያሳየው የመምህራኖቹን ጥያቄ መልሰው እራሳቸው ማስተጋባታቸው ነበር። “የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ የኛን ህይወት የሚቀይር አይደለምና ይህንን የተናገሩት የመንግስት ባለስልጣናት ማስተባበያ ይስጡ” ሲሉ መምህራኖቹ ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን እንዳንረሳው ገና ሁለት ሳምንት አልሞላንም። አቶ መለስም “ያደረግነው የደመወዝ ጭማሪ ሳይሆን የእርከን ማስተካከያ ነው ይህ ደግሞ የመምህራኑን ህይወት አይቀይርም” ሲሉ ተደምጠዋል። ታድያ አቶ መለስ በዚህ ጉዳይ ላይ ከተስማሙ የመምህራኑ ወንጀል ምኑ ላይ ነው? አቶ መለስ አስቀድመው ከራሳቸው ጋር በሰከነ ልቦና መምከር በተገባቸውም ነበር። ምክንያቱም ኢቲቪ ለመምህራን የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ የመምህራኖቹን ህይወት የሚለውጥ ነው ማለቱን እረስተውት ወይም አልተመለከቱት ይሆን?
የአቶ መለስ ንግግር በጥሞና ላዳመጠ “እኚህ ሰውዬ የሚኖሩት በተለየ አለም ነው እንዴ?” የሚያስብል ነው። የስራ ማቆም አድማ ያደረጉት መምህራን የማስተማር ብቃት የሌላቸው ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል። እንግዲህ ስራ በቆመባቸው ትምህርት ቤቶች የነበሩት መምህራን ላይ የብቃት ጥያቄ ከተነሳ በነዛ ትምህርት ቤቶች ትምህርት የቆመው መምህራኖቹ ጥያቄ ሲያነሱ አልነበረም ማለት ነው። መለስ ከጫካ አስተሳሰብ ወጥተው እንደ ሃገር መሪ ማሰብ በተገባቸው ነበር። ይህንን ማድረግ ባይችሉ እንኳን ለፓርላማቸው ክብር ቢኖራቸው መልካም ነበር።   

1 comment:

Anonymous said...

great!