Monday, April 23, 2012

እስክንድር ነጋን ሳስበው ሳስበው …፪


በተመስገን ደሳለኝ
ሰኞ ቀንን ደባሪ ነው ይሉታል-በተለምዶ፡፡ ለጋዜጠኛ ግን ሰኞን ከእሁድ የሚለየው እኩል አለመከሰታቸው ብቻ ነው። በተረፈ በእኛ ሙያ ደባሪ ወይም አስደሳች ቀን የሚለያዩት በስማቸው (ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ዕረቡ…) ተብለው ሳይሆን በየቀኑ በሚከሰተው የዜና እና የመረጃ ክብደት ነው። እናማ ሚያዝያ 1 ቀን 2004 ዓ.ም የዋለው ሰኞ ለእኔ ደባሪ አልነበረም። እንዲያውም በጣም ከተደሰትኩባቸው ጥቂት ቀናቶች አንዱ ነው። ለምን መሰለህ? በጠቀስኩት ዕለት ከአሲምባ (ከመኖሪያ ቤቴ) እንደወጣሁ ለስራ ጉዳይ የቀጠርኳቸው የተለያዩ ሰዎች ስለነበሩ ፈጠን ፈጠን ብዬ ጉዳዬን ለመጨረስ መዋተት ጀመርኩ። ሰአቱም እንዲህ እንዲህ እያለ እኩል ቀን ላይ ደረሰ። እለቱ ብራም ስለነበር መንፈስን አይጨፈግግም። እንዲህ አይነት የአየር ንብረት ደግሞ ዘና ስለሚያደርግ ጥቂት የእግር ጉዞ (ወክ) ለማድረግ ይጋብዛል። እናም የጐዳናውን ጥግ ይዤ አራት ኪሎን ሰንጥቄ ወደ ፒያሳ ድንበር ተጠጋሁ፣ ይህን ጊዜም ድንገት ተንቀሳቃሽ ስልኬ የ‹‹አድምጠኝ›› ኡኡታዋን አሰማች። ለአፍታ ያህልም የተደወለውን ቁጥር አየት አድርጌ ‹‹ሀሎ›› ስል መልስ ሰጠሁ፣ ከመቅፅበትም በደስታ ሲቃ የታፈነ ድምፅ ምላሽ ሰጠኝ። የእስክንድር ነጋ ባለቤት ጋዜጠኛ ሠርካለም ፋሲል ነበረች-የደወለችው፡፡ የደስታዋ ድምፅም በውስጤ ዘለለ። ቦርቅ ቦርቅ፣ ዝለል ዝለል፣ ጨረቃን ንካ ንካ… የሚል ስሜት ወረረኝ። ስልኩን ዘግቼው እንኳ ያ አብሳሪ ድምጽ ማስተጋባቱን አላቋረጠም ‹‹እስክንድርን ፔን ኢንተርናሽናል የ2012 ተሸላሚ ጋዜጠኛ አድርጎ መረጠው፡፡›› ደጋግሞ አቃጨለብኝ፡፡ እናም በጎዳናው ላይ ድምፄ እስኪሰማ ‹‹እስክንድር ጀግና ነህና ይገባሃል!!›› እያልኩ ጮኽኩ፡፡
ጥሎብኝ ጀግና እወዳለሁ። ብዙ ጀግኖች ከልቤ ቀርተዋል። ዳግማዊ ቴዎድሮስ እና ዳግማዊ ምንሊክን ከልብ እወዳቸዋለሁ። ስለ አሉላ አባነጋ እና ዘርአይ ደረሰም ባወራ ባወራ አይሰለቸኝም፡፡ በተለይ ደግሞ ብዙ ለፍቶ ተገቢውን ዋጋ ያላገኘው ዘርአይ ደረስ ከምንም በላይ ያሳዝነኛል። መቼም ዛሬ ዘርአይ በህይወት ቢኖር የሞተላት ኢትዮጵያ ቀኝ ገዢ፣ የተወለደበት ክፍለሀገር ኤርትራ ደግሞ ቀኝ ተገዥ ሆነው ስለተገኙ ተለያይተዋል መባሉን ሲሰማ ምን ሊሆን እንደሚችል ሳስበው ያስደነግጠኛል። አብዲሳ አጋ፣ ጄኔራል ፋንታ በላይ እና ጄኔራል ኃየሎም አርዕያም እንዲሁ ይመቹኛል። እነዚህ እንግዲህ የጦር ጀግና ናቸው። …እንዳልኩህ መንግስቱ ኃ/ማሪያምን እና መለስ ዜናዊን ደግሞ ለመውደድ እና ለመቀበል አስብና አንዳች የሚያስወድድ ምክንያት እያጣሁ ደክሞኝ እተወዋለሁ፡፡ አንዳች እንኳ…
አሜሪካኖቹ እንደሚሉት ሲቪል ጀግኖችም አሉ። ከእነዚህ ሲቪል ጀግኖች ለዘላለም የወደድኩት አንድ ሰው አለ-አበበ ቢቂላ የሚባል። ኦ አቤ የእኔ ጀግና። መቼም አበበ ቢቂላን የማያውቀው የለም። ሌላው ቀርቶ በወቅቱ ‹‹የአፍሪካ አባት›› ተብለው ከተሰየሙት አፄ ኃይለስላሴ የማይተናነስ ስምና ዝና ነበረው። ኧረ እንዲያውም የማታ ማታ የውጭ ሀገር ሰዎች ኢትዮጵያን ያስታውሱበት የነበረው ‹‹የኃይለስላሴ ሀገር›› የምትለው ቅጥያ ‹‹የአበበ ቢቂላ ሀገር›› በሚል እስከመቀየር ደርሶ ነበር። ይህ ብርቱ ሰው በሮም ኦሎምፒክ ማራቶን፣ ያውም በባዶ እገሩ ሮጦ አሸንፎአል። ከአፍሪካ የመጀመሪያው የወርቅ ተሸላሚ ሲሆን ከአለምም 42 ኪሎ ሜትርን በባዶ እግር ሮጦ ያሸነፈ የመጀመሪያው ሰው ነው። አቤ በዛ ኦሎምፒክ ያሸነፈው ማራቶንን ብቻ አይደለም። የጣሊያንን ወራሪን የቅኝ ገዥ መንፈስም ነው። የውድድሩ ዕርቀት የሮም አደባባይን መዞርን ያካትት ነበር። በሮም አደባባይ ደግሞ ከኢትዮጵያ የተወሰደው የአክሱም ሀውልት (በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል) ተገትሮአል። ምንም እንኳ ሀውልቱ የጣሊያንን ዘራፊነት መስካሪ ቢሆንም፣ ጣሊያኖች ግን የአሸናፊነታቸው ወይም የአድዋን ሽንፈት በቀል ለመወጣታቸው መገለጫ አድርገው ያዩት ነበር። እናም አቤ ሀውልቱ ጋር ሲደርስ በጣም ፍጥነት ጨመረ። ይህን የታዘበው ጋዜጠኛም ውድድሩ ከአለቀ በኋላ አቤን ጠየቀው ‹‹ሀውልቱ ጋ ስትደርስ ምን ተሰማህ?›› አቤም መለሰ ‹‹ደም ፍላቴ መጣ!›› እነሆ ይህ ከሆነ ከብዙ አመት በኋላ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹‹የአክሱም ሀውልት ለወላይታው ምኑ ነው?›› አሉና አረፉት። በዚህ አባባላቸውም እነ አቤ ሀውልቱ እንደማይመለከታቸው አረዱን። እርግጥ ይህ ፖለቲካ ነው። ሆኖም ጥሩ ያልሆነ ፖለቲካ ስለመሆኑ ግን አንዳች ጥርጣሬ አይግባህ።
የሆነ ሆኖ አቤ በሮም የጀመረውን ድል በቶኪዮም ደግሞታል። ይህ ብቻ አይደለም የአካል ጉዳት ከደረሰበት በኋላም በዊልቸር ተወዳድሮ አሸንፎአል። አይበገሬነት ይሉሃልም ይሄ ነው፤ ሌላ አይደለም። እስክንድር ነጋ ማለትም ይህ ነው፣ ሌላ አይደለም። ታስሮም እንኳ አለም ያከበረው፡፡
መቼም ስለዚህ ብርቱ ሰው መፃፍ በራሱ ደስታን ይፈጥራል። ዛሬ እስር ቤት ከገባ ስምንተኛ ወሩን ይዞአል፤ በታሰረ በ10ኛው ቀን በታተመችው ፍትህ ጋዜጣ ላይ ‹‹እስክንድር ነጋን ሳስበው፣ ሳስበው…›› በሚል ርዕስ ስለወጣው ዳገት፣ ስለከፈለው ዋጋ፣ በምርጫ 97 ማግስት ከነፍሰጡር ባለቤቱ ጋር በቃሊቲ እስር ቤት መግባቱን፣ ባለቤቱም በዛው እስር ቤት የመጀመሪያቸውን ወንድ ልጅ እንደተገላገለች… ፅፌልህ እንደነበር ታስታውሳለህ፡፡ እነሆ ዛሬ ደግሞ ክፍል ሁለትን ልፅፍልህ የተነሳሁት የአለም አቀፍ ተሸላሚ መሆኑን ተከትዬ ነው። ዜናው በይፋ የተገለፀው የዛሬ ሳምንት ነው።
እንዳልኩህ እስክንድር ነጋ ተራ ጋዜጠኛ ወይም ተራ ተንታኝ አይደለም። ለእኔ ከእነ አሉላ አባነጋ፣ ከእነ ዘርዕይ ደረስ፣ ከእነ አብዲሳ አጋ ትይዩ የሚቆም የሀገር ባለውለታ ነው። ሲቪል ጀግና ነው፡፡ ‹‹የያዝኩትን መሬት እንዳልቅ›› የመንፈስ ብርታት የሆነኝም ይህ ሰው ነው። በዚህ ሰው ዘመን ተገኝተህ፣ በዚህ ሰው ሙያ መሰማራት ደግሞ ምን ያህል ልብ እንደሚያሞቅ ልነገርህ አልችልም። ልክ ፕሌቶ የተባለው ግሪካዊ ፈላስፋ ‹‹ከምንም በላይ ሶቅራጥስ በነበረበት ዘመን እንድኖር ስላደረከኝ አመሰግናሃለሁ›› እንዳለው አይነት ምስገናም በልቤ አቀረብኩ፡፡
በእርግጥ እስክንድር ዛሬ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ነው። ወደቃሊቲ ከመላኩ በፊት ማዕከላዊ ነበረ። ማዕከላዊ የታሰሩ እስረኞች በወዳጅ ዘመድ እንዲጠየቁ ተፈቅዶላቸው ሳለም እሱ አልተፈቀደለትምና ‹‹አይዞህ›› ለማለት እንኳ አልቻልኩም። እናም ለወራት አላየሁትም። ከታሰረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜም ያገኘሁት ቃሊቲ ከሄደ በኋላ ነው። ነገር ግን በቃሊቲ ሳገኘው በአካል ከእስሩ በፊት የማውቀውን እስክንድርን አልነበረም፡፡ የመንፈስ ጥንካሬው ያልተለየውና የሞራል ልዕልናው እንዳለ ቢሆንም አካሉ ተጎሳቁሏል። ፊቱ ጠልሽቷል። ሰውነቱ በእጅጉ ከስቷል፡፡ እመነኝ ገፅታውን ገና እንዳየከው የማታውቀው ሀዘን ከልብህ ይሰነቀራል። አንዳች ያህል ምሬትም አፍህን ይሞላዋል። በዚህ ላይ ገና ‹‹ክፉና ደግ›› ያለየ የአምስት አመት ልጁ አብሮኝ ስለነበረ የአባትና የልጅ ናፍቆት እና ፍቅር ልውውጥን ለመመልከት በእጅጉ ጠንካራ መሆንን ይጠይቃል። እምባ እንዳይፈስ መታገልንም ይፈልጋል። ስሜትህ ይደፈርሳል። ያጥወለውልሀል። በተለይ የአባትየው የበኹር ልጁን አንገቱ ስር ወሽቆ ግብግብ ሲል ማየት ብቻ ለዘላለም ከአይነ ህሊና የማይጠፋ የስቃይ ስሜት ይፈጥርብሃል።
የሆነ ሆኖ ናፍቆትን ከአንገቱ ስር እንደሸጎጠው ጥቂት ቃላቶችን ተለዋወጥን።
‹‹ምን ሆነህ ነው ሰውነትህ የተጎሳቆለው?››
‹‹ማዕከላዊ እያለሁ አሞኝ ነበር››
‹‹ታዲያ አሁን እንዴት ነህ?››
‹‹በጣም ሰላም ነኝ፣ ተሽሎኛል። ፍትህ እንዴት ነች? ማዕከላዊ እያለሁ አገኛት ነበር። እዚህ ግን ስለማይፈቀድ አላገኛትም››
‹‹ደህና ነች። ስለክሱ ምን እያሰብክ ነው?››
‹‹ክሱ ምንም ይሁን ምን አያሳስበኝም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ እስክንድር ነጋ አሸባሪ እንዳልሆነ ያውቃል። አንተም ታውቀኛለህ››
‹‹አውቅሃለሁ። ለሀገርህ ከላይ ታች ስትል ህይወትህን በቅጡ እንዳልኖርክም አውቃለሁ። ብቻ አይዞህ በርታ››
‹‹ለእኔ አታስብ አንተ በርታ። ስራህን በጥንካሬ ስራ››
ይህንን ጊዜ ጭውውታችንን ጠጋ ብሎ ያደምጥ የነበረው የማረሚያ ቤቱ ፖሊስ ‹‹በቃ! ሰዓት ደርሶአል›› ሲል በትህትና አቋረጠን፡፡ ሆኖም በዚህ መሀል በፍጥነት ስለክሱ፣ እንዲሁም ድንገት ፍርድ ቤቱ ተከላከል ቢባል እንኳ እውነቱን የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቀው ዘንድ እንዴት መከላከል እንዳለበት ስለመከላከያ ምስክሮቹ አውርተን ተለያየን።
ምሬት በልቤ እንደገባ የወህኒ ቤቱን ግቢ ለቀኩ። …ብዙ ነገርም አሰብኩ፣ ብዙ ነገር… ግና ምን ማድረግ ይቻላል? ለራሴ የጠየኩት ጥያቄ ነው። እኛስ ብንሆን እስከመቼ ነው ‹‹እከሌ ታሰረ፣ እከሌ በይቅርታ ተፈታ፣ እከሊት ተፈረደባት… እያልን ዜና ስንሰራ የምንውለው? በዚህ አጀንዳስ ሰለምንድን ነው ‹ቢዚ› እንድንሆን የተደረግነው? እኮ ሀገሩን የሚወድ፣ ለሀገሩ ራዕይ ያለው እየታሰረ፣ ራዕይ የሌለው እያሰረ እስከመቼ…›› ያጨናነቁኝ ጥያቄዎች ቢሆኑም ምላሽ እንደሌላቸው አውቃለሁ። እለቱ ደባሪ ሆነብኝ። የእስክንድር ገፅታ፣ ከልጁ ናፍቆት ጋር ናፍቆቱን ለመወጣት ያደርግ የነበረው ነገር በሙሉ ደጋግሞ እየመጣብኝ ቀኔን ብልሽትሽት አደረገው። ደግነቱ የቱንም ያህል ብከፋ፣ የቱንም ያህል ባዝን፣ የቱንም ያህል… ተስፋ የመቁረጥ ስሜት አይመጣብኝም። ይህማ እንዴት ይሆናል? ጉዳዩ የሀገር ጉዳይስ አይደል እንዴ? ያውም የምንወዳት ኢትዮጵያ፡፡ (መቼም ኢትዮጵያውን ለኢትዮጵያ መሞታቸው እንደሁ ዛሬም አላቋረጠም፡፡ ዘላለማቸውን ለትግል የተፈጠሩ ያልተሳካላቸው ታጋዮች… ዳሩ የሀገር አንድነት ሲናጋ እና አንዱ ብሄር በሌላው ላይ እንዲነሳ የሚጋብዝ ፖለቲካ በስራ ላይ ሲውል ካልሞትን መቼ ልንሞት ነው? አዎ! አሊያማ ‹‹ኢትዮጵያ የእኛ መመኪያ…›› ዘፈን ብቻ ሆኖ ሊቀር ነው?)
የሆነ ሆኖ በቀጣዩ ሳምንትም ይህን ጀግና ለመጠየቅ አስቤ ለባለቤቱ አብረን እንሄድ ዘንድ ደወልኩላት። ሆኖም የመለሰችልኝ መልስ ምድርና ሰማዩን አዞረብኝ። ነገር አለሙ ድብልቅልቅ አለብኝ። የጋዜጠኛ ሠርካለም አጭር መልስ እንዲህ የሚል ነበር፡-
‹‹ውይ! ተሜ ባለፈው ጠይቀከው ከሄድክ በኋላ ከእኔ፣ ከልጁ እና ከአንዲት ዘመዳችን በስተቀር ማንም ሰው እንዳይጠይቀው ተደርጓል!››
አሁን ጩኽ፣ ጩኽ… አለኝ። ግና ምን ብዬ ልጩኽ? ወደማንስ ነው የምጮኸው? አምስት ልጆች የወለደችለትን የሰማኒያ ሚስቱን በመጥረቢያ ጨፍጭፎ የገደለ ወይም በጠራራ ፀሐይ ማጅራት ሲመታ የተያዘ… ያለገደብ በወዳጅ ዘመድ ሲጠየቅ፤ ከእነ አብዲሳ አጋ እና ዘርዐይ ደረስ ተርታ የሚሰለፈው የሀገር ባለውለታ እስክንድር ነጋ በሶስት ሰው ብቻ፤ እሱም በውስን ሰዓት (ከሰኞ እስከ አርብ ለ10 ደቂቃ፣ ቅዳሜ እና እሁድ ለ30 ደቂቃ) እዚህ ሀገር ምንድር ነው እየተደረገ ያለው? በዚህ ሁኔታ እስከ መቼ ነው የምንዘልቀው? 40 ወይስ 50 አመት? በሀገሪቱ ህገ-መንግስት መሰረት እንኳ ‹‹መታሰር›› የማይቻልበት ሁኔታስ ወዴት ያደርሰናል? አስረው ሲያበቁ ጠያቂ መገደብ፣ ሲያሻው በእስረኛ ማስደብደብ.. ታዲያ የትኛው ነው ህጋዊ? ታሳሪው ወይስ አሳሪው? መልሱልኛ?
ደግሞ እኮ ጉዳዩን የከፋ የሚያደርገው ይህ አይነቱ አሰራር ነባር መሆኑ ነው። ማንም ይሁን ማን፣ የቱንም ያህል ለሀገር የለፋ ይሁን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ተቃዋሚ ከሆነ እንኳንም ቆሞ ሞቶም አድሎ እና በደል አይቀርለትም። ለዚህም ማጠናከሪያ የሚሆን አንድ ምሳሌ እንይ።
ደህና! በእድሜዬ በሀገር ባለውለታዎች ስርዓተ ቀብር ላይ የተገኘሁት ለሁለት ሰው ብቻ ነው። ለፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ እና ለእጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሚትር አርቲስት አፍወርቅ ተክሌ (በእርግጥ በስራ ምክንያት ሳይመቸኝ ቀርቶ ቀብራቸው ላይ መገኘት ያልቻልኩባቸው አንድ ሶስት የሀገር ባለውለታዎች ነበሩ፤ ባለመቅበሬ ዛሬም ድረስ ይቆጨኛል)
ሆኖም የእነዚህ ሁለት ሰዎች የቀብር ስነ ስርዓት ጉራሜይሌ ነው። እንዴት አይነት ጉራማይሌ ይሆን? ለምሳሌ ፕሮፌሰር አስራት ወ/የስ አርበኛ ናቸው። አርበኛ ብቻም እንዳይመስሉህ ይልቁንም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን በፕሬዝዳንትነት የመሩ፣ ለ40 ዓመት ከአፍሪካ ምርጥ የቀዶ ጥገና ሀኪም ሆነው ሳለ ከሀገራቸው ኢትዮጵያ ሳይወጡ ያገለገሉ ናቸው። ነገር ግን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ተቃዋሚ በመሆናቸው እና ኤርትራን አታስገንጥሉ፣ አንዱን ብሔር በሌላው ላይ አነሳስታችሁ አታጨራርሱ… በማለታቸው እስር ቤት ገቡ። በእስር ቤትም በጠና ታመው ሳለ በቂ ህክምና ሳያገኙ ቀርተው ነፍሳቸው ከስጋቸው ልትለይ ሰዓታት ሲቀር ለህክምና እንዲወጡ ፈቅደናል የሚል ቧልትን ተከትሎ እንዲወጡ ተደረገ፤ ህይወታቸውም በዛው አለፈ። ስርዓት ቀብራቸው ግን እንደብዙዎቻችን እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡ ሌላው ቀርቶ የአርበኞች መቀበሪያ በሆነው የቅድስት ስላሴ ካቴድራል እንኳ እንዲቀበሩ አልተፈቀደላቸውም። እናም በባለወልድ ቤተክርስቲያን ተቀበሩ። ወዳጄ! ኢህአዴግ ከጠላህ እንዲህ ነው፤ ሬሳህንም ቢሆን አይለቀውም፡፡
አሁን ደግሞ እጅግ ወደ ተከበሩ ሎሬት ሚትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የቀብር ስነስርዓት እንመለስ። መንግስት በይፋ ኮሚቴ አዋቅሮ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ጀምሮ ሁሉም ሚኒስትሮች የአበባ ጉንጉን ልከው፣ ስርዓተ ቀብሩ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሽፋን አግኝቶ በስላሴ ካቴድራል የቀብር ስነስርዓታቸው ተፈፅሟል። ይህ ሁሉ ስርዓትም ሆነ የመንግስት ተሳትፎ ለአርቲስቱ ቢያንሳቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይደለም። ምክንያቱም አፈወርቅ ኢትዮጵያን ያስጠሩ ታላቅ ባለውለተኛ ናቸውና የቀብር ስርዓታቸው ከዚህ በተሻለ ሁኔታም ቢደምቅ የሚከፋ አይኖርም፡፡
ጥያቄው ግን ሌላ ነው። ለምሳሌ አፈወርቅ አንድም ቀን ፖለቲካ ውስጥ (በተቃውሞም በድጋፍም) ገብተው አያውቁም። እናም በኢህአዴግ ‹‹ጥቁር መዝገብ›› ውስጥ ስማቸው የለም፡፡ ችግር ይኖር የነበረው በዚህ መዝገብ ቢሰፍሩ ነበር፡፡ አዎን! አፈወርቅ ተክሌ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ተቃዋሚ ቢሆኑ ኖሮስ? ብለን ካሰብን እመነኝ ቀብራቸው እንዲህ ሊሆን ቀርቶ ከፕሮፌሰሩም ያነሰ ይሆን ነበር። አየህ! ይህ ነው የሚደብረው። ይህ ነው መንግስትና ፓርቲ የተደበላለቀበት ፖለቲካ ማለት፡፡ ምክንያቱም አፈወርቅ የኢህአዴግ ተቃዋሚ ቢሆኑ እንኳ ይህ ሁሉ የሀገር ባለውለታነታቸውም ሆነ የአለም ምርጥ ሰውነታቸው ሊቀንስ ወይም ሊሰረዝ አይችልም። ፖለቲካ ሌላ ነው። ሀገር ደግሞ ከዛ የሰፋ ትልቅ ነገር ነው። ሚዛኑ እንደ መንግስት እንጂ እንደ ፓርቲ ሊታይ አይገባውም። አስራት ወልደየስ የቱንም ያህል የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ተቃዋሚ ቢሆኑም አርበኝነታቸው፣ ዩኒቨርስቲውን በፕሬዚዳንትነት መምራታቸው እና ለ40 አመታት ሀገራቸውን ከማገልገላቸው ጋር አንዳች የሚያያዘው ነገር የለም። ከተያየዘ ግን መጥፎ ነው፡፡ መጥፎ ፖለቲካም ይሉሃል ይህ ነው። የመንግስትን እና የፓርቲን ሚና መደበላለቅ። በእርግጥ የዚህ አይነቱ ፖለቲካ ሰለባ አስራት ወልደየስ ብቻ አይደሉም፡፡ ባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህንም ናቸው፡፡ ልክ እኮ ነኝ! የእኒህ አንጋፋ የጥበብ ሰው ሞት ለኢህአዴግ ከዊትኒ ሆስተን ሳይቀር ያነሰ ነበር፡፡ ምክንያቱም የዊትኒ ሞት በመንግስት ሚዲያ የተጋነነ ሽፋን ሲያገኝ የሎሬትን ግን ያነሳውም የለ፤ ለምን መሰለህ ዊትኒ ከላይ በነገርኩህ መዝገብ ውስጥ ስሟ የለም፡፡ ፀጋዬ ገብረመድን ግን ሀገሬን አትከፋፍሉ፣ ኢትዮጵያዬን አትግደሉ፣ ታሪካችንን አታበላሹ… ያሉት ነገር በዛ በጥላቻ መዝገብ እንዲሰፍሩ አድርጎአቸዋልና ነው፡፡
የእስክንድርም ጉዳይ እንዲሁ ነው። እስክንድር በምንም ወንጀል ተጠርጥሮ ይታሰር፤ ነገር ግን ህገ መንግስቱ ከሰጠው የታሳሪዎች መብት አንዳች ሊሸረፍበት አይገባም። የመሽረፍም ስልጣን ያለው የለም፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ ህግ-መንግስቱ ጉራማይሌ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ በተግባር ሲሸርፈው ‹‹ህጋዊ ነው›› ወይም ‹‹ሽብርተኝነትን ለመከላከል ነው›› የሚሉት ፈሊጥ በሰበብነት ይቀርባል፡፡ በግልባጩ ደግሞ ተቃዋሚዎች በሀሳብ ‹‹ሲሸርፉት›› ወይም ‹‹ይህ አንቀፅ ኢትዮጵያን ይከፋፍላልና ለህዝበ ውሳኔ ይቅረብ›› ሲሉ ሽብርተኝነት ነው ይልሀልና የኢህአዴግ የጫወታ ህግ ፡፡
ሌላ ጉራማይሌ
ደህና! ሌላ ጉራማይሌ እንይ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ‹‹እስክንድር ነጋ አሸባሪ ነው›› ሲል አስሮታል። በሌላ በኩል ደግሞ አለም አቀፍ ‹‹የፀሀፊዎች ነፃነት›› ተቆርቋሪ የሆነው “Pen International” ሚያዚያ 5 ቀን 2004 ዓ.ም. “Journalist Eskinder Nega wins 2012 PEN Freedom Award” በሚል ርዕስ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እስክንድር ነጋን ‹‹a leading advocate for press freedom and freedom of expression in Ethiopia (በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት እና ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብት እንዲከበር በመሪነት የተጋ)›› ሲል አሞካሽቶታል። ፔተር ጎድዊን የተባሉ በአሜሪካ የፔን ኢንተርናሽናል ማዕከል ሊቀመንበርም እስክንድርን የገለፁት እንዲህ ሲሉ ነው፡-
“The Ethiopian writer Eskinder Nega is that bravest and most admirable of writers, one who picked up his pen to write things that he knew would surely put him at grave risk.”
(ኢትዮጵያዊው ፀሐፊ እስክንድር ነጋ ደፋርና በእጅጉ የሚደነቅ ፀሐፊ ነው። ብዕሩን ሲያነሳ የሚፅፍባቸው ነገሮች በእርግጠኝነት አደገኛ አደጋ ሊያመጡበት እንደሚችሉ ሁሉ ያውቃል)
የ“Freedom to write program” ዳይሬክተር ላሪ ሳይመሰ ለእስክንድር ያላቸውን አድናቆት የገለፁት “He is truly an extraordinary individual (እጅግ ልዩ ሰው)” ሲሉ ነበር።
የፔን ኢንተርናሽናል መግለጫ እንደሚያትተው እስከዛሬ ድረስ 46 ሰዎች የዚህ ሽልማት ተሸላሚ ሲሆኑ፣ 37ቱ በእስር ላይ ሳሉ የተሸለሙ ቢሆንም፣ ከእነዚህ እስረኛ ተሸላሚዎች መሀከል 33ቱ እንደተሸለሙ ወዲያውኑ ከእስር ተለቀዋል። እናስ! እስክንድር ይህን ቁጥር በአንድ ይጨምረው ይሆን?
እንግዲህ እስሩን ጉራማይሌ የሚያደርገው፣ ፖለቲካውን ደግሞ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ የሚከተው ይህ ነው። እናም መልስ የሚያስፈልገው ጥያቄ ከዚህ ቅርቃር የምንወጣው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ይከበር ዘንድ የተጉትን በማሰር እና በማሳደድ ወይስ በአሸባሪነት ከሶ ወህኒ በመወርወር? የሚለው ነው። እርግጥ ነው የዚህን ጥያቄ መልስ የሚያውቁት የስርዓቱ መሪዎች ብቻ ናቸው።

No comments: