Saturday, April 28, 2012

በቴዲ አፍሮና በአዲካ መካከል አለመግባባት ተፈጠረ


ሪፖርተር 
ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከአዲካ ኮሙዩኒኬሽንና ኢቨንትስ ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባቱን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡
ቴዎድሮስና አዲካ ውዝግብ ውስጥ የገቡት ‹‹ጥቁር ሰው›› በተሰኘው የቴዎድሮስ አዲሱ አልበም ከስፖንሰርና ከሽያጭ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ቴዲ አፍሮና አዲካ መጋቢት 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ባደረጉት ውል፣ ቴዎድሮስ የአልበሙን ዋና ሲዲ (ማስተር ሲዲ) በአራት ሚሊዮን ብር ሸጧል፡፡ ክፍያውም በሁለት ጊዜ ተፈጽሟል፡፡ 

በዚህ ውል መሠረት አዲካ ያወጣውን ሙሉ ወጪ ከመለሰ በኋላ ከሚገኘው የተጣራ ትርፍ ቴዎድሮስ 20 በመቶ ገቢ ያገኛል፡፡ ይህም ለአምስት ዓመታት የሚቀጥል ሆኖ፣ ከአምስት ዓመት በኋላ በሲዲው ላይ ያለው ሙሉ መብት ከአዲካ ወደ ቴዎድሮስ ይዛወራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በውሉ መሠረት አዲካ ስፖንሰር የመፈለግና በህትመቱ ላይም የስፖንሰሩን ማስታወቂያ የመጠቀም መብት ይሰጠዋል፡፡ በቴዲና በአዲካ መካከል በዋናነት አለመግባባቶች የተፈጠሩት በእነዚህ ነጥቦች ዙርያ ሲሆን፣ አለመግባባታቸውም እየከረረ መምጣቱን ምንጮች እየገለጹ ነው፡፡ በአለመግባባቱ ውስጥም የሦስትዮሽ ውል የፈረመው ቤሌማ ኢንተርቴይመንት ኩባንያም ሌላኛው ተዋናይ ነው፡፡

ለቴዲ ቅርብ የሆኑ የመረጃ ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ቴዲ በሲዲው ላይ የሜታ ቢራ ማስታወቂያ ይለጠፋል ብሎ አላሰበም፡፡ ነገር ግን ሲዲው በሚታተምበት ወቅት የሜታ ቢራ ማስታወቂያ በዋናው ሲዲ ላይ ተለጥፎ የተመለከተው ቴዲ ‹‹ሙዚቃዬን ትልልቅ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናትም ያዳምጡታል፤ ለሕፃናቱ የመጠጥ አርዓያ መሆን አልፈልግም፤›› የሚል ሐሳብ በመሰንዘሩ፣ የሜታ ቢራ ማስታወቂያ የተለጠፈበት ኮፒ እንዲወገድ ብሎም ለገበያ እንዳይቀርብ ስምምነት ላይ ይደረሳል፡፡ በቴዲ በኩል ያሉ መረጃዎች የሜታ ቢራ ዓርማ የተለጠፈባቸው ሲዲዎች ብዛት 120 ሺሕ ነው ቢባልም፣ በአዲካ በኩል ግን 87 ሺሕ ኮፒዎች ናቸው፡፡

‹‹በውላችን መሠረት የስፖንሰሩ ጉዳይ ይመለከተናል፤ ለእኛ ግን ምንም የቀረበልን ሐሳብ የለም፤›› ሲሉ የቤሌማ ኢንተርቴይመንት ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወሰን አበጀ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሚያዝያ 6 ቀን 2004 ዓ.ም. ለሚሠራጨው ሲዲ ማስተር ሲዲውን አሥር ቀን እየቀረው የተረከበው አዲካ፣ ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶበታል በሚል ሲዲው ላይ ያለውን የሜታ ማስታወቂያ በማርከር በማጥፋት ለገበያ አቅርቧል፡፡ ይህ የተደረገው ብቸኛው ስፖንሰር የተባለው የሜታ ቢራ ፋብሪካ ይሁንታ በመገኘቱ ነው ሲሉ፣ የአዲካ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አዋድ መሐመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በገበያ ውስጥ ይህ የተደለዘ ሲዲ መሠራጨቱን የተመለከተው ቴዲ በሁኔታው ደስተኛ አለመሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሌላኛው አለመግባባት ቴዎድሮስ የታተመውን የሲዲ ቁጥር ማወቅ አለመቻሉ ነው ተብሏል፡፡ የቴዎድሮስን ሐሳብ አቶ ወሰንም ይጋራሉ፡፡ 

ቴዲና አዲካ ባላቸው ስምምነት መሠረት ‹‹ጥቁር ሰው›› አልበም ከሚያስገኘው የተጣራ ትርፍ ገቢ ውስጥ 20 በመቶ ለቴዲ አፍሮ የሚከፈል ነው፡፡ የተጣራ ትርፍ መኖሩን ለማወቅ ከሚያገለግሉ ነገሮች አንዱ የታተመውን የሲዲ ቁጥር ማወቅ ነው፡፡ በመጀመርያዎቹ የህትመት ወቅቶች የተዘረጋው የሞባይል አጭር መልዕክት (SMS) ሲላክ የሚጻፍ ሲሪያል ቁጥር ታትሞበታል፡፡ ቴዎድሮስ የሲርያል ቁጥሩ ቢቀጥል የታተመውን የሲዲ ብዛት ማወቅ ያስችላል ብሎ ያምናል፡፡

በሚቀጥሉት የሲዲ ህትመቶች ግን ምንም ዓይነት ሲሪያል ቁጥር ታትሞ ለገበያ እንዳልቀረበ የሪፖርተር መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡ በተዘዋዋሪ መንገድ ከቴዎድሮስ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ቴዎድሮስ ሙሉ ትኩረቱን ሙዚቃው ላይ ከማድረጉ ባሻገር የቢዝነስ ሥራዎችን ማኔጀሩ አቶ አዲስ ገሠሠ ያካሂዳሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን ቴዎድሮስ በሁኔታው ደስተኛ አለመሆኑን ገልጿል፡፡

ቴዎድሮስ ዝርዝር መረጃዎችን ከማኔጀሩ ማግኘት እንደሚቻል ቢገልጽም፣ የሪፖርተር መረጃዎች እንደሚሉት ቴዎድሮስና ማኔጀሩ መግባባት ተስኗቸዋል፡፡ ከማኔጀሩ ከአቶ አዲስ ገሠሠ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከቴዎድሮስ ጋር መግባባት ያልተቻለው ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በቴዲ የመቃወሚያ ነጥቦች አዲካ ኮሙዩኒኬሽን በፍፁም እንደማይስማማና ይልቁንም የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ርቀት መሄዱን፣ የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አዋድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በመጀመርያ አዲካ የሜታ ቢራን ማስታወቂያ በሲዲው ላይ ለማተም የውል ስምምነቱ ይፈቅድለታል፡፡ ‹‹ነገር ግን ቴዎድሮስ ሕፃናት ሙዚቃዬን ይሰማሉ ማለቱን እንደ መልካም ነገር ወስደን ከሲዲው ላይ አጥፍተነዋል፡፡ ካለን ጊዜ አንፃር ሲዲው ጥቅም ላይ እንዳይውል ቢባልም በደረስንበት ወቅታዊ ስምምነት ማስታወቂያውን አጥፍተን ገበያ ላይ አውለነዋል፤›› ሲሉ አቶ አዋድ ገልጸዋል፡፡

‹‹ሲዲው ለገበያ የሚቀርብበት በጣት የሚቆጠሩ ጊዜያት ብቻ ነበሩን፤ ጊዜ ወሳኝ ነበር፤›› ሲሉ አቶ አዋድ የወቅቱን አንገብጋቢነት አስረድተዋል፡፡ ማሽኑ በቀን የማተም አቅሙ ከ20 ሺሕ እስከ 25 ሺሕ ሲዲ ነው፡፡ በዚህ የማምረት አቅም የሜታ ማስታወቂያ የተለጠፈበትን 87 ሺሕ ኮፒ ማስወገድ የሚቻል ነገር አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ሲሪያል ቁጥር የተሰጠው ለግጥሞቹ ነው ተብሎ አዲካ፣ የኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበርና የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በመተባበር ማንኛውም ሰው ኦሪጂናል መግዛቱ የሚታወቅበትና በዚህም የሚሸለምበት አሠራር ነው የተዘረጋው ያሉት አቶ አዋድ፣ ‹‹በነበሩን ጥሩ የሥራ ግንኙነቶች ምክንያት ብሔራዊ ሎተሪ ፈቃድ እንደሚሰጥ ታሳቢ ተደርጎ ህትመት ቢጀመርም፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ ብሔራዊ ሎተሪ ፈቃድ ከልክሏል፤›› ሲሉ የሲሪያል ቁጥር በመጀመርያዎቹ ህትመቶች መካተቱንና በተከታዮቹ ህትመቶች ላይ መቋረጡን ያስረዳሉ፡፡

‹‹የሲሪያል ቁጥር የታተመው የሲዲ ኮፒ ብዛቱን ለማወቅ አይደለም፤›› ሲሉ አቶ አዋድ ይገልጻሉ፡፡ አንድ ባዶ ሲዲ የሚገዛው በአራት ብር ነው፡፡ የሲዲ መሸፈኛ (ከቨር) አምስት ብር ነው፡፡ የግጥሙ ህትመት ዋጋውም የዚያኑ ያህል ነው፡፡ ከአንድ ሲዲ የሚገኘው ትርፍ ስድስት ብር ነው፡፡ በእስካሁኑ ሒደት የታተመው ሲዲ የወጣበት ወጪ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን፣ አዲካ ሙሉ ወጪውን ከሸፈነ በኋላ ከሚያገኘው የተጣራ ትርፍ ውስጥ 20 በመቶው ለቴዎድሮስ ገቢ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን የካሴት ህትመቱ የትና እንዴት እንደተካሄደ ለቴዲ እንቆቅልሽ ሆኖበታል፡፡ ለገበያ ቀረበ የተባለውን የሲዲ ቁጥር እንደማያምንበት ቴዎድሮስ ተናግሯል፡፡ ቴዎድሮስ ከውጭ አገር የታተመ ሲዲ ገብቷል ብሎ ከማመኑም በተጨማሪ፣ ለውጭው ዓለም በምን መንገድ ሲዲው እንደተሠራጨ አሁንም ቴዲ ይጠይቃል፡፡

አቶ አዋድ ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች በተመሰከረለት ባለሙያ ኦዲት ይደረግ መባሉን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ሒደትም ላይ ኤችኤስቲ የተሰኘው ኩባንያ ተመርጦ ወደ ኦዲቲንግ ሥራ በመግባት ላይ እያለ ቴዎድሮስ ኦዲቲንጉ እንዲቆም ማድረጉ ተሰምቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ወገኖች አለመግባባት በጡዘት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ አካላት በሽምግልና ለመገላገል እየሞከሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

Friday, April 27, 2012

ሰርካለም ፋሲል የባለቤቷን የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሽልማት ልትቀበል ነው


አዲስ ቪው ሚዲያ
ኤፕሪል 27 2012
የ2012 PEN/Barbara Goldsmith Freedom to Write Award አሸናፊ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሽልማት ላይ ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል እንደምትገኝ የአዲስ ቪው ምንጮች ገለጹ።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በሽብርተኝነት ተከሶ ጉዳዩን በፍርድ ቤት እየተከታተለ ባለበት ወቅት “ፔን ፍሪደም አዋርድ” የተባለውን አለም አቀፍ ሽልማትን አግኝቷ።ፔን አሜሪካን ሴንተር  የተባለው አለማቀፍ ድርጅት ጋዜጠኛ እስክንድር ለሰራቸው ስራዎች እውቅና በመስጠት ለ26ኛውን ሽልማት  ለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል

ፔን አሜሪካን ሴንተር  ባዘጋጀው እና ሜይ 1 2012 በኒውዮርክ ሲቲ American Museum of Natural History በሚካሄደው የሽልማት ፕሮግራም ላይ የጋዜጠኛ እስክንድር ባለቤት ጋዜጠኛ ሰርካልም ተጋባዥ ሆና እንደምትገኝ እና ሽልማቱንም ትቀበላለች ተብሎ ይጠበቃል።

ከሰርካለም በተጨማሪ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ የሆኑ ድርጅት ሀላፊዎች እንዲሁም የቀድሞ አንድነት ሊቀመንበር የነበሩት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የዝግጅቱ ታዳሚዎች እንደሚሆኑ ታውቋል። ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል በ2007 Courage in Journalism Award የተሰኘውን ሸልማት ከ  IWMF (International Women's Media Foundation) ማግኘቷ እና ከሽልማቱ ያገኘችውን ገንዘብ ለአምንስቲ ኢንተርናሽናል መለገሷ ይታወሳል።     

Thursday, April 26, 2012

ህዝባዊ ዓመፀን በዲጅታል ዘመን ጥቅም ላይ ማዋል


ደ ብርሃን ሚድያ
26 April ፳፩፪ 

ገነ ሻርፕ (Gene Sharp ) ሃይል ያልተቀላቀለበትን ህዝባዊ አመፀ/ ንቅናቄ  ካጠኑት      ሰዎች ግንባር ቀደሙ ነው። አንድአንድ  ሰዎች የሻርፕ መፀሃፍት በአለፉት ሃያ አመታት ወስጥ በነበሩት ለውጦች ወስጥ ሰፊ ሚና ነበራቸው ይላሉ፣ ከሚሎሶቪች አስከ ሙባረክ ውድቀት ድረስ።  "ሃይል ያልተቀላቀለበት ንቅናቄ ዘዴዎች" በሚለው ማኗሉ  ሻርፕ መቶ ዘጠናስምንት ዘዴዎችን ይዘረዝራል (list of 198 methods )። እነዚህ አምባገነን መንግስቶቺን መጣያ ዘዴዎች ደግሞ በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላሉ :- ሃይል ያልተቀላቀለበት ተቃውሞ አና ግፊት ማሳደር፣ አለመተባበርና ሃይል  ያልተቀላቀለበት ጣልቃ ገብነት ናቸው። እነዚሕ  ዘዴዎች ዛሬም ድረስ ጠቃሚ ቢሆኑም በዘመነ  ዲጅታል/ ኮምፒዩተር  አነዚሕኑ ዘዴዎች ከወቅቱ ጋር ማስኬድ ብሎም አዳዲስ  ዘዴዎቺን መፍጠሩ ጠቃሚ ነው ።

የሻርፕን መቶ  ዘጠናስምንት ዘዴዎች  መሰረት በማድረግ ታዋቂው የአይ ሪቭኦውሊሽን ድሕረ ገጸ   አዘጋጅ ዶክተር ፓትሪክ ሜር  አና ባልደረባው አንዴት አነዚሕን ዘዴዎች በዘመነ  ዲጅታል/ኮምፒዩተር  አንዴት ማሳደግ አንደሚቻል የሚጠቁም ዶከመንት አዘጋጀተዋል። አርሶም አነዚሕኑ ዘዴዎች ያንብቡ፣ ለወዳጆቸዎት ሁሉ ያስነበቡ አንዲሁም አርሶም አነዚሕን ዘዴዎች አንዴት ማሳደግ አንደሚቻል ያሎትን ሃሳብ ሳይን አፕ በማረግ ያኑሩ። 
ወደ ዳታቤዙ ወስጥ ለመግባት ይሄን    ጠቅ ያርጉ ። 

http://www.debirhan.com/2012/04/blog-post.html

Tuesday, April 24, 2012

በአዲስ አበባ አንድ ወጣት እራሱን ማቃጠሉ ተሰማ


ሚያዚያ ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አንድ ጎልማሳ ኢትዮጵያዊ ዛሬ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ በመሐል አዲስ አበባ ጊዮርጊስ ዳግማዊ ምኒልክ ሃውልት ፊት- ለፊት በሚገኘው የአውቶብስ መቆሚያ ጎዳና ፤ አዲስ ምሩቅ ተማሪዎች የሥራ ማስታወቂያ የሚመለከቱበት ቦታ ላይ ራሱን በላስቲክ የውሃ መያዣ በያዘው ቤንዚን አቃጠለ፡፡
በሥፍራው የነበሩ ሰዎች በውሃ እና ለፍራፍሬ ንግድ ከለላ የተደረገ ህንፃ ሲሰራ እንደ ከለላ የሚጠቀሙበት ሸራ መሰል ነገር፤ በማንሳትና በማራገፍ እሳቱን ሊያጠፉለት ቢሞክሩም ግለሰቡ ተውኝ መሞት መፈለጌን ህዝብና መንግሥት እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ ብሏል ሲሉ የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
እንደ እማኞች ገለፃ ግለሰቡ ከወገቡ በላይ ሙሉ በሙሉ ተቃጥሎ ቆዳው የተኮማተረ ሲሆን ጀርባው በእሳቱ በእጅጉ የተጎዳ ሲሆን፣ ጸጉሩም መርገፍ ጀምሮ አይኑ ብቻ ከጉዳት ተርፏል፡፡
ዘጋቢያችን 11፡ 30 ሰዓት ላይ ከሥፍራው ሲደርስ ራሱን ያቃጠለው ግለሰብ የለበሰው ጃኬት እንደ ወረቀት አሮ ወዳድቆ፣ ወይን ጠጅ ነጠብጣብ ያለው የተቃጠለ ሸሚዝ ቁርጥራጭ ወዳድቆ የተመለከተ ሲሆን ግለሰቡን ፌዴራል ፖሊስ በፓትሮል መኪና መወሰዱን እማኞች ነግረውት የቀይ መስቀል አምፑላን መጥቶ ፖሊስ ወስዶታል ተብሎ ባዶውን ሲመለስ ከሥፍራው ታዝቧል፡፡
ዘጋቢያችን ከሥፍራው በእቡእ እማኞችን ለማናገር የሞከረ ሲሆን ሁኔታውን እየሰቀጠጣቸው የተመለከቱ በአካባቢው የጋዜጣ፣ የመጽሔት ንግድ ላይ የነበሩ እማኞች ሰውየው ከታክሲ መውረዱንና በወቅቱ በአኳ ላስቲክ የያዘው ቤንዚን ሳይሆን ውሃ እንደመሰላቸውና ንግግርም ሲያደርግ ትኩረት እንዳልሰጡት ገልጸዋል፡፡
ቤንዚኑን ራሱ ላይ በመላ አካላቱ እያፈሰሰ ሁለት ጊዜ ክብሪት ሲጭር እምቢ ብሎት በሦስተኛው ቦግ ብሎ መንደድ እንደጀመረና እየሮጠ ወደ አውቶብስ ተጠጋ በማለት የገለጹት እማኞች፣ የአውቶብስ ሹፌር በሮቹን ዘግቶበት ተመልሶ የማስታወቂያ መመልከቻው ቦታ ላይ ተዝለፍልፎ በመውደቁ ሰዎች እየተሯሯጡ ውሃ በማፍሰስ እና በሸራ በመጠቅለል ሊያጠፉለት ቢሞክሩም እስትንፋሱ ሙሉ ለሙሉ ባይጠፋም ጉዳቱ ከፍተኛ ሆኗልብለዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስም ወደ ሥፍራው በፍጥነት በመምጣት ሰዎችን በትኖ የሚያጣጥረውን ግለሰብ በፓትሮል መኪና በመውሰድ በአካባቢው በቅርብ የተመለከቱ ሰዎችን ሰብስቦ እዚያው አካባቢ የሚገኝ አንድ ቅጥር ጊቢ ሰብስቦ የሞባይል ስልካቸውን በመንጠቅና በማስፈራራት ጊቢውን ዘግቶ አግቷቸዋል ብለዋል፡፡
በአካባቢው የሥራ ማስታወቂያ ስትመለከት የነበረች አንዲት ግለሰብ ጎልማሳው በሰውነቱ ደህና የሚባል ሰው ሲሆን ጸአዳ ስኒከር ጫማ ግሬይ ጅንስ ሱሪና ወይን ጠጅ ሸሚዝ ከጃኬት ጋር መልበሱን በእድሜውም ከ25 እስከ 35 ሊደርስ እንደሚችል ለዘጋቢያችን ገልፃ ከታክሲ ወይም ከባስ መውረዱን ያዩት ሰዎች ነግረውኛል እኔ ግን ሲቃጠል ብቻ ነው የተመለከትኩት ስትል እንባ እየተተናነቃት ለዘጋቢያችን ገልጻለች፡፡
ዘጋቢያችን በቦታው ባደረገው ቅኝት ግለሰቡ ወደቀ የተባለበት ሥፍራው ላይ የልብሶቹ ቁርጥራጮችን፣ እሳቱን ሊያጠፉበት የሞከሩትን ሸራ መሳይ ላይለን፣ በውሃ የረጠበ ሥፍራ ተመልክቷል፤ የፌዴራል ፖሊስም ሰዎችን አግቶ እና አንድ ግለሰብን ደግሞ (እማኞች በሞባይል ለመቅረጽ ሞክሮ ነበር ብለዋል) አንበርክከው ሲመቱት ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሪፖርተርና የካሜራ ጋዜጠኛ በሥፍራው ተገኝተው ቦታውን ቀርጸው ሁኔታውን የተመለከቱ ሴት እማኞችን ቃለ መጠይቅ ያደረጉ ሲሆን የደህንነት ሰዎች መጥተው እንዳይቀርጹ ሲከለክሏቸው እኛ ኢቲቪዎች ነን ሥራችንን እንስራበት በማለት ቀረፃቸውንና ቃለ- መጠይቃቸውን የቀጠሉ ሲሆን የደህንነት ሠራተኞቹም ለዘብ ብለው ሰዎችን ወደ መበተኑና ወደ መጠጋጋቱ ሲያመሩ ዘጋቢያችን አስተውሏል፡፡

Eritreans are asking:" Is Isaias dead or alive?"

ADDIS ABABA (Reuters) – Eritrea has sought to quash speculation about President Isaias Afewerki’s health, saying he was “fit as a fiddle” and lambasting the United States for spreading “lies” over his condition.

Rumours have been rife in the past few years that Isaias, 66 and in power since 1993 after leading his country to independence from Ethiopia, was in poor health and required regular trips abroad for treatment.
Speculation about his health has stirred up debate over who might eventually replace the reclusive leader. Isaias has no obvious successor but the opposition says he might be grooming his son, Abraham, for the top job.

U.S. diplomatic cables released by WikiLeaks have also mentioned the possibility of the military elite trying to take over power in the Red Sea state.
Eritrea refuted speculation about his health late on Sunday in a special announcement aired by the information ministry on state television and later broadcast on the Internet.
“There has been widespread speculation in the past few weeks that President Isaias has fallen seriously ill,” the broadcast said.
“We would like to announce that President Isaias is fit as a fiddle and is in the best of health under all criteria,” it added in remarks translated from the Tigrinya language.
Eritrea’s exiled opposition has alleged on numerous occasions that the president is suffering from a serious liver ailment and that he has been receiving medical attention in Qatar, with which his nation has close ties.
In a move aimed at highlighting his good health, the broadcast showed a montage of Isaias sporting a baseball cap and making a short dash down a dirt track as he waved to bystanders in light rain.
It also pictured the leader snapping pictures with a point-and-shoot camera, then walking up a slope and posing as he smiled alongside other men on the banks of a reservoir.
Eritrea accused the U.S. Central Intelligence Agency (CIA) of spreading the “lies” surrounding its leader’s health.
In a leaked cable from the U.S. embassy in the capital Asmara, former U.S. ambassador Ronald McMullen said Isaias feared the U.S. would try to kill him by firing a missile on his residence in the coastal city of Massawa.
Asmara often criticises Washington which it says backs its arch rival Ethiopia in the two countries’ frontier dispute.
“Those lies emanate from Langley with the CIA being the rumour-mongers,” said the television announcement, referring to the intelligence agency’s headquarters.
Eritrea and Ethiopia have been at loggerheads since their 1998-2000 border war, which killed 70,000 people, and they accuse one another of backing the other’s rebels and working to topple the other’s government.
Isaias accused Washington last month of plotting Ethiopian cross-border raids that targeted alleged rebel camps.
(Editing by George Obulutsa and Maria Golovnina)

Monday, April 23, 2012

መንግስት ሙስሊሙ ያቀረበውን ጥያቄ በሀይል ለመፍታት ቆርጦ ተነስቷል


ኢሳት ዜና:-ከሳምንት ሳምንት እየተጠናከረ የመጣው የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ፣ መላው ክርስቲያኖችንን እንዲያካትት ጥሪ እየተላለፈ ባለበት በአሁኑ ወቅት መንግስት ችግሩን በሰላም ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የሀይል አማራጭን ለመጠቀም ፍላጎት እያሳየ ነው።
የአቶ መለስ ዜናዊን የሰሞኑን የፓርላማ ንግግር ተከትሎ በመላ አገሪቱ የሚገኙ በርካታ ሙስሊሞች ባለፈው አርብ ተቃውሞዓቸውን ካሰሙ በሁዋላ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከመንግስት ጋር በመተባባር ጥያቄውን በሀይል ለመፍታት ፍላጎት አሳይቷል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ከተለያዩ የክልል ኡላማዎች፣ ከዞን እና ከወረዳ ምክር ቤት ሀላፊዎች ጋር በጋራ ተመካክሮ ባሳለፈው አቋም ፣ አክራሪነት መንፈስ የተጠናወታቸው  አካላት ህዝበ ሙስሊሙ ሀይማኖቱን ተረጋግቶ እንዳያካሂድ እያደረጉት በመሆኑ ፣ ህብረተሰቡና የጸጥታ አስከባሪዎች ግለሰቦቹን እየያዙ ለህግ ማቅረብ እንዳለባቸው ውሳኔ አሳልፎአል። 
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ አህመዲን ሼህ አብዱላሂ ባለድርሻዎች አክራሪዎችን እየመረጡ ወደ ህግ እንዲያቀርቡዋቸው ጠይቀዋል።
የኢሳት የዜና ምንጮች እንደሚገልጡት ከሆነ በእየሳምንቱ የሚታየው የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ኢህአዴግንና ደጋፊዎችን፣ መንግስትን እና ተከታይ ኡላማዎችን በእጅጉ እያስደነገጠ ነው። የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ሁለት ምርጫዎች አሉት፣ አንድም ሙስሊሙ የሚያቀርበው ጥያቄ የብዙሀኑ ጥያቄ መሆኑን ተረድቶ ለጥያቄው አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት፣ ሌላም ጥያቄው የጥቂቶች ነው በሚል በሀይል ለመጨፍለቅ መሞከር ነው።
አንደኛው አማራጭ እውን ከሆነ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህዝብም ትልቅ ትምህርት ጥሎ ያልፋል የሚሉት ተንታኞች፣ መንግስት በህዝብ ግፊት ጥያቄዎችን መመለስ ከጀመረ ሌሎችም በተመሳሳይ መልኩ ጥያቄያቸውን እየያዙ ለመቅረብ ድፍረቱን ያገኛሉ ይላሉ። መንግስት ጥያቄውን በሰላም ለመመለስ ከፈቀደ ከሁሉም በላይ ተጠቃሚው መንግስት ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ይሆናል፣ ምክንያቱም ህዝብ በጋራ ከተነሳ መንግስትን ማስገደድ እንደሚችል ቱኒዚያ፣ ግብጽ፣ ወይም ሊቢያ ድረስ ሳይጓዝ በራሱ አገር ጥሩ ትምህርት ይቀስማል፣ ቀዳዳውም እየሰፋ ሌሎችም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ለማቅረብ ይደፋፈራሉ ይላሉ።
ተንታኞቹ እንደሚሉት መንግስት ጥያቄውን በሀይል ለመጨፍለቅ ከሞከረም፣ መላው ሙስሊም በጋራ እና በቁጭት እንዲነሳ እንደሚያደርገው እስካሁን የተከተለውን ፍጽም ሰላማዊ ተቃውሞ ወደ ሀይል ተቃውሞ ሊቀይረውና ደም መፋሰስ ሊከተል እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ። ሙስሊሙ ህብረተሰብ በጀመረው ፍጹም ሰላማዊ ትግል መቀጠሉ መንግስት የሚያስደነብረው ይሆናል ሲሉም ያክላሉ።
በሌላ በኩል ግን ሙስሊሙ ያቀረበው ጥያቄ ብሄራዊ አጀንዳ እንዲኖረውና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ ካስፈለገ፣ ሙስሊሙን ከክርስቲያኑ ለማጋጨት በአቶ መለስ መንግስት የተሸረበውን የመከፋፈል ሴራ ማክሸፍ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር መሆኑን አንዳንድ ተንታኞች ይናገራሉ። አቶ መለስ በሰሞኑ የፓርላማ ንግግራቸው ክርስቲያኑ ህዝብ ደንብሮ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ለማድረግ ቢሞክሩም፣ በሙስሊም ሆነ በክርስቲያኑ በኩል ያጋጠማቸው ተቃውሞ እንጅ ድጋፍ አለመሆኑን ተንታኞች ይገልጣሉ። ክርሰቲያኑ ህዝብ አቶ መለስ ገዳማትን ሳይቀር ለማውደም ሲሞክሩ እያየ ለእርሳቸው ቅስቀሳ ጆሮ አይሰጥም የሚሉት ተንታኞች፣ ይሁን እንጅ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄያቸው በዘላቂነት ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ከፈለጉ ክርስቲያኑን ወገን ለማቀፍ ጥረት ማድረግ አለባቸው። የሙስሊሙ ጥያቄ በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው አገራዊ ችግሮች ሲፈቱ በመሆኑ፣ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ለእነዚህ አገራዊ ችግሮች ቅድሚያ በመስጠት መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ  የሚያሳትፍ መርሀ ግብር ሊነድፉ እንደሚገባ ያሰምሩበታል።
መንግስት በሚወስደው እርምጃ ግራ መጋባቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሰሞኑን የተወሰኑ ሙስሊሞችን ለማሰር እንቅስቃሴ ቢያደርግም አዝማሚያው ስላስፈራው መልሶ ለቋቸዋል።

የቴዲ አፍሮ አልበም ሽያጭ ሬከርድ አስመዘገበ

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የተለቀቀው የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ጥቁር ሰው›› አልበም በ300 ሺሕ ሲዲና በ120 ሺሕ ካሴት ሽያጭ፣ በአጠቃላይ ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አሥር ሚሊዮን ብር ገደማ በማስገባት፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ ታሪክ አዲስ ሬከርድ ማስመዝገቡ ታወቀ፡፡ ሽያጩ የተመዘገበው አልበሙን ከአዲካ ኮሙዩኒኬሽንና ኢቨንትስ ተቀብለው በማከፋፈል እየሸጡ ካሉት ከኤሌክትራና ከአምባሰል ሙዚቃ ቤቶች፣ እንዲሁም ከጣና ኢንተርቴይንመንት ነው፡፡ ኤሌክትራና አምባሰል ሙዚቃ ቤቶች በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች ለሽያጭ ሲያቀርቡ፣ ጣና ኢንተርቴይንመንት በሰሜን ኢትዮጵያ ያከፋፍላል፡፡ 

አዲካ ለሙዚቃ ቤቶቹ እያንዳንዱን ሲዲ በብር 17.50 እያንዳንዱን ካሴት ደግሞ በዘጠኝ ብር ሲያስረክብ፣ ገበያው ውስጥ አንዱ ሲዲ 25 ብር አንዱ ካሴት ደግሞ 13 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ አንዱ ሲዲ በተወሰነለት ዋጋ እንዲሸጥ ቢታሰብም በየመንገዱ እስከ ሃምሳ ብር እንደተሸጠ ታውቋል፡፡ 

አዲካ ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከሽያጮቹ 6.3 ሚሊዮን ብር ያገኘ ሲሆን፣ ቀሪው ገንዘብ ደግሞ ለሙዚቃ ቤቶቹና መንገድ ላይ ለሚሸጡ ገቢ ይሆናል፡፡ አልበሙ ከወጣበት ሚያዝያ 6 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በብዛት እየተሸጠ መሆኑም ታውቋል፡፡ 
በተለይም አልበሙ በወጣበት ሚያዝያ 6 ቀን በርካታ ሰዎች በሙዚቃ ቤቶች ደጃፍ ወረፋ ሲጠብቁና ሌሎችም መንገድ ላይ ካሉ ሻጮች በጭማሪ ዋጋ ሲገዙ ታይተዋል፡፡ 

‹‹በተለያዩ ሚዲያዎች የሙዚቃ አፍቃሪያን ከተወሰነው ዋጋ በላይ አውጥተው አልበሙን እንዳይገዙ ብናስታውቅም፣ አንዳንድ ነጋዴዎች እጥረት ያለ አስመስለው ከተተመነው ዋጋ በላይ ሲሸጡ ነበር፤›› በማለት የአዲካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ዘለቀ ገልጸዋል፡፡ 

አቶ አሸናፊ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ 500 ሺሕ ሲዲዎችና 200 ሺሕ ካሴቶች ሙዚቃ ቤቶቹ እንደሚያስፈልጋቸው በመጀመርያ ስላስታወቁ አልበሙ አሁንም እየታተመ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አልበሙ በአዲካ ወኪሎች በኩል በውጭ አገር በመሸጥ ላይ ቢሆንም፣ አቶ አሸናፊ ግን ምን ያህል ኮፒዎች አንደተሸጡ ገና አልታወቀም ብለዋል፡፡ 

ከአሁን ቀደም ለገበያ ከቀረቡ የሙዚቃ ሥራዎች ከፍተኛ ሽያጭ በማስመዝገብ የአገሪቱን ሬከርድ ይዟል የተባለለት የቴዲ አፍሮ አልበም መሆኑን በሙዚቃው ዘርፍ ውስጥ ያሉ ይስማማሉ፡፡ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ እንኳን 300 ሺሕ ሲዲ መሸጥ ይቅርና ኦሪጂናል አልበም ለመሸጥ ከፍተኛ ችግር እንደነበር በሙዚቃ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ይስማሙበታል፡፡ 

በተለይም ከቅጂ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በርካታ የሙዚቃ ሰዎች ተስፋ እስከ መቁረጥ መድረሳቸውም ይታወሳል፡፡ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የሙዚቃ ባለሙያ፣ ‹‹የቴዲ አፍሮ አልበም ሽያጭ የአገሪቱ ሬከርድ ሲሆን፣ ምናልባት ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ኢንዱስትሪም ዓይን ከፋች ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ አልበሙ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ቢያገኝም እሳቸው ግን በግላቸው የተለየ አመለካከት እንዳላቸው ገልጸው፣ ዝርዝር ውስጥ ገብተው ከመናገር እንደሚቆጠቡ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሕዝብ ሆ ብሎ የተቀበለውን ነገር ለመተቸት መነሳት ለጊዜው አስፈላጊ አይደለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡


ሪፖርተር እንደዘገበው